የታዋቂው ፖለቲከኛ የሺዋስ አሰፋ ሁለት ልጆች በአውሮፕላን በረራና በልብ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አራት መጻህፍትን አስመረቁ

248

መስከረም 29 ቀን 2015 (ኢዜአ) የታዋቂው ፖለቲከኛ የሺዋስ አሰፋ ሁለት ልጆች በአውሮፕላን በረራና በልብ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ አራት መጻሕፍትን ትናንት በአዲስ አበባ አስመርቀዋል፡፡

ታዳጊዎች ልዩ ዝንባሌያቸውን እንዲያውቁ የወላጆች እና የመምህራን ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ታዳጊ ህሊና የሺዋስ እና ቅዱስ የሽዋስ ተናግረዋል፡፡

መጻህፍቱ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች የተጻፉ ናቸው።

የ9ኛ ክፍል ተማሪዋ ታዳጊ ህሊና የሺዋስ በአማርኛ "ስለ ልብ የተነገሩ ምርጥ አባባሎች" እና በእንግሊዘኛ "አናቶሚ ኤንድ ፊዚዮሎጂ ኦፍ ዘ ኸርት" የሚሉ ሁለት መጻህፍትን ጽፋለች፡፡

ወንድሟ ቅዱስ የሺዋስ አሰፋ ደግሞ "ዘ ፈንዳሜንታልስ ኦፍ ኤርፕሌን ዲዛይን" እና "የአውሮፕላን የበረራ ሚስጠሮች" የሚሉ ሁለት መጻህፍትን ለአንባቢዎች አብቅቷል።፡

ታዳጊ ህሊና፣ ዝንባሌዋንና ተሰጥኦዋን ለማግኘት ብዙ ጊዜ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን ጠቅሳ፤ አሁን መክሊቷ የልብ ስፔሻሊስትነት ሆኖ እንዳገኘችው  ገልጻለች፡፡

በዚህም ከትምህርቷ ጎን ለጎን ዝንባሌዋን ለማሳካትም በልብ ዙሪያ ብዙ እውቀት ያላቸውን ምህራን በመጠየቅና በመምህራን እገዛ በልብ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጻህትን መድረሷን ተናግራለች፡፡

ታዳጊ ቅዱስ የሽዋስ በበኩሉ ስለ አውሮፕላን መመራመር የጀመረው እና ዝንባሌውን ያገኘው  ገና በህጻንነቱ እንደሆነ ይናገራል፡፡

በ2024 ዓ.ም የራሱ ቀለል ያለች አውሮፕላን የመስራት ዓላማ ይዞ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁሞ፤ ወላጆች ልጆቻቸው ዝንባሌያቸውን እንዲያገኙ ማገዝ አለባቸው ነው ብሏል።

የታዳጊዎቹ አባት ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው ወላጆች የልጆቻቸውን ህልም አውቀው ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለልጅቻቸው ስኬት ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡

ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚቸገሩት ተሰጥኦዋቸውን ማወቅ ላይ ነው ያሉት አቶ የሽዋስ፤ በዚህም መስራት የሚገባቸውን ስራ ሳይሰሩ ያልፋሉ ብለዋል፡፡

ስለዚህ የነገ የኢትዮጵያ ተረካቢ የሆኑ ህጻናት ለአገር እድገት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ ዛሬ ላይ ዝንባሌያቸውንና መክሊታቸውን እንዲያገኙ ተገቢውን እገዛ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም