ዩኒቨርሲቲው በተሟሏ ዝግጅት ተፈታኞችን መቀበሉንና በመውሊድ በዓል ምክንያት የዘገዩ ተማሪዎችም ዛሬ ተጠቃለው እየገቡ መሆኑን ገለጸ

179

መስከረም 29 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተሟሏ ዝግጅት ተፈታኞችን መቀበሉንና በመውሊድ በዓል ምክንያት የዘገዩ ተማሪዎችም ዛሬ ተጠቃለው እየገቡ መሆኑን ገለጸ።

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት መሰጠቱ ኩረጃን ለመከላከልና በራሱ የሚተማመን ብቁ ዜጋ ለማፍራት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተገልጿል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ፈተና በባሕሪው የእውቀት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ምቹ የፈተና ስፍራና የስነ ልቦና ዝግጅት ይፈልጋል።

ለዚህም ዩኒቨርሲቲው የመኝታ ከፍሎች፣ የመመገቢያ አዳራሾችና ምቹ የፈተና ቦታዎች በማዘጋጀት ተፈታኞችን መቀበሉን ጠቁመዋል።

አብዛኛው ተፈታኝ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲው መግባቱን ጠቁመው፤ በመውሊድ በዓል ምክንያት የዘገዩ ተማሪዎችም ዛሬ ተጠቃለው እንደሚገቡ ገልጸዋል።

የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የትውልድ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ፈተናው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰጠቱ ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ በአስተማማኝ ሁኔታ ፈተናቸውን እንዲወስዱና በራሳቸው እውቀት ሰርተው ውጤታቸውን እንዲጠብቁ የሚያደርግ መሆኑን በመጠቆም።

ከዚሁ ጎን ለጎንም ተፈታኞች በቆይታቸው በቀጣይ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገቡ ሊገጥሟቸው የሚችሉ ሁኔታዎችን ከወዲሁ እንዲረዱ ያግዛል ነው ያሉት።

ብሄራዊ ፈተናው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ መደረጉ በየደረጃዉ የሚሰጠው ትምህርት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆንም ሰፊ መሰረት የሚጥል መሆኑንም ነው ያነሱት።

ትምህርት ቤቶች ብቁ ዜጋን ለማፍራት እየሔዱበት ያለውን ርቀት ለመለካት የሚያስችል ሲሆን ተማሪው በተገቢው መንገድ ተዘጋጅቶ ፈተና ላይ እንዲቀመጥ ያስችላል ብለዋል።

ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ብቁ የሆኑ መምህራንን ለማፍራት ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ የአሁኑ የፈተና አሰጣጥ ሒደት ለዚሁ ተግባር ሰፊ እገዛ ያደርጋል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም