በክልሉ በጀትን በአግባቡ በመጠቀም የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ መስራት ይገባል---የበጀትና ፋይናስ ቋሚ ኮሜቴ

120

ደብረ ብርሃን መስከረም 28/2015 (ኢዜአ) ---ለክልሉ የተመደበውን በጀት በአግባቡ በመጠቀም የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት መስራት ይገባል ሲል የአማራ ክልል ምክር ቤት የበጀትና ፋይናስ ቋሚ ኮሜቴ አሳሰበ።

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ በየደረጃ ከሚገኙ ገንዘብ መምሪያ ሃላፊዎችና ማኔጅመት አባላት ጋር በደብረ ብርሃን ከተማ እየመከረ ነው።

በምክር ቤቱ የበጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሜቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዓለም ዋጋየ እንዳሉት፣ ክልሉ በጦርነት ውስጥ ቢሆንም የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየተሰራ ነው።

የህዝብን የልማት ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ከመንግስትና መንግስታዊ ካለሆኑ ድርጅቶች የሚመደበውን ውስን ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ገልፀዋል።

"የህዝብ የልማት ጥያቄዎች እንዲመለሱም በየደረጃው የሚገኘው አመራር በሃላፊነትና በቁርጠኝነት ስሜት መስራት ይኖርበታል" ሲሉም አሳስበዋል።

"ልማትን ለማፋጠን ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ ይገባል" ያሉት ሰብሳቢዋ፤ በጀት ሳይያዝ ከፍተኛ የልማት ፕሮጀክቶችን ማቀድ ተገቢ እንዳልሆነና በጀትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ጥላሁን መሐሪ በበኩላቸው እንዳሉት፣ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ አልሞ በከፈተው ጦርነት በክልሉ ሰፊ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት አድርሷል።

ጉዳቱን በመቋቋም ዘላቂ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የ2015 በጀት ግብርናን፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስተሪና መሰል ዋና ዋና ዘርፎችን ታሳቢ በማድረግ የተደለደለ መሆኑን አስረድተዋል።

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የክልሉን ልማት በመደገፍ በኩል ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልፀው፣  ድርጅቶቹ በ2014 ዓ.ም 16 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በመመደብ በተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች መሳተፋቸውን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ዶክተር ጥላሁን እንዳሉት በክልሉ ባሉ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች 17 ቢሊዮን ብር የሚሆን ተከፋይና ተሰብሳቢ ሂሳብ አለ።

ይህንን ገንዘብ አሟጦ ለመሰብሰብ መረጃ የማደራጀት ሥራ እየተሰራ ይገኛል።

የክልሉ መንግስት ለልማት ባለው ቁርጠኝነት በኢንቨስትመንት ዘርፍ ከ545 በላይ ፕሮጀከቶች መኖራቸውን የተናገሩት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት የከተማዋን እድገት ለማፋጠን መንግስትና የግል ባለሀብቱ የተቀናጀ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ።

የደቡብ ወሎ ዞን ገንዘብ መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ እቴነሽ ጌታቸው በበኩላቸው በተያዘው በጀት ዓመት የአሸባሪውን ህወሓት ሴራ ከመመከት ጎን ለጎን በጀትን በአግባቡ በመጠቀም የህዝብን የልማት ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአማራ ክልል ለበጀት ዓመቱ የልማት ሥራዎች ማስፈፀሚያ ከ95 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡ የሚታወስ ነው።

ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው በእዚህ መድረክ ከክልሉ የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች እና የሥራ ሃላፊዎች የተሳተፉ ሲሆን በ2014 ዕቅድ አፈጻጸምና የ2015 ዕቅድ ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም