ኮሌጁ በማታና በተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎች አስመረቀ

85

ሚዛን አማን (ኢዜአ) መስከረም 28/2015 የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ በማታና በተከታታይ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ከ1ሺህ በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ።

ዛሬ የተመረቁት ተማሪዎች በእንስሳት፣ በእጽዋትና በተፈጥሮ ሀብት የትምህርት መስኮች በደረጃ 4 ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ መሆናቸውም ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በሳይንሳዊ እውቀት በመደገፍ በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑንም ኮሌጁ አስታውቋል።


የኮሌጁ ዲን አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በምረቃት ስነ-ስርዓቱ ወቅት ኢትዮጵያ የያዘችውን የልማት ውጥን ለማሳካት ኮሌጁ በግብርናው ዘርፍ ብቁ ዜጋን የማፍራት ሀገራዊ ተልዕኮ ወስዶ እየሰራ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ለግብርና ዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ዘርፉን በምርምና ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ምሩቃኑም ሀገሪቱ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ብዝሃ ሕይወት ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር ለሀገር ዕድገት ውጤታማ ሥራ እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።

እንደሀገር የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግም ምሩቃን በኮሌጁ የቀሰሙትን አውቀት ተጠቅመው የድርሻቸውን አንዲወጡም አሳስበዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሽመልስ መኩሪያ "ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ያረጋገጠችና የበለጸገች ሀገር እንድትሆን እንደሀገር ለሚከናወኑ ስራዎች ተመራቂዎች የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

በዘርፉ የበለጠ ስኬት እንዲመዘገብም ምሩቃኑ ለአርሶ አደሩ ተገቢውን ሙያዊ እገዛ እንዲያደርጉም ሃላፊው ጠይቀዋል።

የሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ 1994 ዓ.ም ተመስርቶ ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያሰለጠነ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም