በአስተዳደሩ ስንዴን በመኸርና በበጋ በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው

89

ላል ይበላ (ኢዜአ) መስከረም 28/2015--- በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስንዴን በመኸርና በበጋ በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን የብሔረሰቡ አስተዳደር አስታወቀ።

በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የ2015 የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ በላል ይበላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ስቡህ ገበያው በመድረኩ እንዳሉት፣ በብሔረሰብ አስተዳደሩ በመኸርና በበጋ የስንዴ ልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሰራ ነው።

"የዋግ ማህበረሰብ ከእህል እርዳታ እንዲላቀቅ አርሶአደሩን በቅርበት በማገዝ የበጋ ስንዴ ልማትን በአግባቡ እንዲያከናውን ማድረግ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

"የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ በግብርናው ዘርፍ እየተሰራ ያለው ተግባር አበራታች ነው'' ያሉት አቶ ስቡህው፣ ባለድርሻ አካላትም ለበጋ መስኖ ልማት ትኩረት እንዲሰጡ አስገንዝበዋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ በበኩላቸው "በምግብ ራስን መቻል የሚለውን ሀገራዊ ግብ መሰረት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ በአስተዳደሩ በስፋት ይከናወናል" ብለዋል።

በቀጣይ ከእርዳታ እህል ተረጂነት ነፃ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አይነተኛ አማራጭ መሆኑንም አስረድተዋል።

በብሔረሰብ አስተዳደሩ በበጋ መስኖ ከሚለማው 3ሺህ 252 ሄክታር መሬት ውስጥ 2ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ የበጋ ስንዴን በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አዲስ እንዳሉት በአንደኛና በሁለተኛ ዙር የበጋ መስኖ ልማት ከ9ሺህ 200 በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 94ሺህ ኩንታል የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል።

"ለመስኖ ልማቱ ስኬታማነት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ካሉ 600 የውሃ መሳቢያ ፓምፓች በተጨማሪ 470 አዲስ ተጨማሪ የውሃ መሳቢያ የሞተር ፓምፓች ለአርሶ አደሩ ይቀርባሉ" ብለዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በተሻለ ለማከናውን አርሶ አደሩ የተሳተፈበት የመስኖ ንቅናቄ መድረክ መካሄዱን የተናገሩት ደግሞ የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ ወርቁ ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት በወረዳው የበጋ ስንዴን በመስኖ ለማልማት 550 ሄክታር መሬት ተለይቶ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል።

በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ዕቅድ ትውውቁ መድረክ ላይ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም