በዓሉን የሀገራችን ሰላምና አንድነት እንዲጠናከር ፈጣሪን አበክረን በመለመን እያከበርን ነው -የእስልምና እምነት ተከታዮች

124

ሐረር፤ መስከረም 28/2015(ኢዜአ)፡- የመውሊድ በዓልን የሀገራችን ሰላምና አንድነት እንዲጠናከር ፈጣሪን አበክረን በመለመን እያከበርን ነው ሲሉ በሐረር ከተማ የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ።

1ሺህ 497ኛው የነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዓ.ወ) የመውሊድ በዓል በሐረር ከተማ  የእምነቱ ተከታዮች ነብዩን በማወደስ  በድምቀት  እያከበሩ  ይገኛል ፡፡

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ሼክ ጀማል ሙህየዲን እንደገለጹት፤ በዓሉን እርስ በእርስ በመደጋገፍናያላቸው ለሌላቸው በማከፈል እያከበሩ ነው፡፡

የመውሊድ በዓል  በህዝቡ መካከል የነበረውን አንድነት ፣አብሮነት እና የመረዳዳት እሰቶች ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ እየተከበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በዓሉ  በጋራ የሚያከብሩትና በህዝቦች መካከል  አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን አመለክተው፤ በዓሉን ስናከበር ለሀገር ሰላም መረጋገጥ አበክረን ፈጣሪን  በመለመን ብሎም የአካባቢ  ፀጥታን በመጠበቅ ልናደርገው ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡

ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ሃጂ በሃር አብዱረህማን በበኩላቸው፤   የነብዩን ፈለግ በመከተል ድሆችን በማብላት  ለሰላም ዘብ በመቆም በዓሉን  እያከበርነው እንገኛለን ብለዋል ፡፡

በዓሉን በጎዳናዎች ላይ በመንቀሳቀስ ነብዩን እያወደሱና የተቸገሩ ወገኖችን እየረዱ እያሳለፉ እንደሚገኙ የተናገረው ደግሞ  ወጣት አብዱረዛቅ ኡመር  ነው።

የመውሊድ በዓልን የአካባቢው ብሎም የሀገር ሰላም ፣ የህዝቦች አንድነትና ልማት እንዲጠናከር ፈጣሪን አበክሮ በመለመን ማክበሩን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች  ለሀገራችን ሰላም ፣አንድነትና  ልማት መቆማችንን  አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲልም መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም