ህዝቡ በዓሉን ሲያከብር የአብሮነት እሴቶችን በማጠናከርና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል

134

ጎንደር  መስከረም 28/2015 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር የአብሮነት እሴቶችን ለማጠናከርና የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት ሊሆን እንደሚገባ የጎንደር ከተማ ኡለማ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሸህ ኢብራሂም መሀመድ አሳሳቡ፡፡

1ሺህ 497ኛው የነብዩ መሀመድ የመውሊድ በዓል የእምነቱ ተከታዮች በከተማው ጀሚያል ካቢር ታላቁ መስጅድ ዛሬ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች አክብረዋል፡፡

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ እንደተናገሩት ጎንደር ከተማና አካባቢዋ የሃይማኖቶች አብሮነትን መሰረት አድርገው የሚኖሩበት ጥንታዊና ታሪካዊ ሥፍራ ነው፡፡

ሙስሊምና ክርስቲያኑ ዘመናትን የዘለቀ የአብሮነት እሴቶች የገነቡ ሃይማኖቶች መሆናቸውን ጠቅሰው ፤ሆኖም በሃይማኖት ሽፋን ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ሁለቱ የእምነት ተከታዮች በሰከነ መንገድ ተወያይተው በመፍታት ዳግም አብሮነትን ማስቀጠል መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ታላቁ የነብዩ መሃመድ በዓል ሲከበርም እርስ በእስር በመዋደድና በመከባበር ያለው ለሌለው በመረዳዳትና በመተጋገዝ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

''ህዝብ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሃይማኖታዊ አስተምሮውን በተግባር ማስመስከር አለበት ያሉት ደግሞ የከተማው እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሃፊ አቶ መሀመድ ማሩ ናቸው፡፡

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩ አቡሃይ በበኩላቸው ጎንደር የሃይማኖት መቻቻል፣ የአብሮነትና የአንድነት ከተማ እንድትሆን ህዝበ ሙስሊሙ ላደረገው በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በከተማው በሃይማኖት ሽፋን ድብቅ ዓላማቸውን ለማስፈጸም ያለሙ አካላት የለኮሱትን እሳት በማክሸፍ በማውገዝና ሰላሙን በማስጠበቅ የህዝብ ሙስሊሙ የድርሻውን መወጣቱን ገልጸዋል፡፡

ሙስሊሙ ማህብረሰብ የሀገር የልማትና የሰላም ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከሌሎች እምነት ተከታይ ወንድሞችና እህቶቹ ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ በአብሮነት እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተጎዱ ወገኖች በመደገፍ፣ የወደሙ ተቋማትን መልሶ በማቋቋም ከሙስሊሙ ማህብረሰብና ከእምነቱ መሪዎች ጋር የጀመረው ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የእምነቱ ተከታዮችና መሪዎች በዓሉን ደም በመለገስ፣ ቁራን በመቅራትና በሌሎች ሃይማኖቱ በሚፈቅዳቸው ስነ-ስረአቶች በዓሉን አክብረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም