በዲላ ከተማ የሚገኙ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት የመውሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ2 ሺህ ሰዎች ማዕድ አጋሩ

130

ዲላ መስከረም 28/2015 (ኢዜአ) የዲላ ከተማ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት 1 ሺህ 497ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዓ.ወ) የመውሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ2 ሺህ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የበዓል መዋያ ማዕድ አጋሩ።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህሉን ከማዳበር ባለፈ ለሀገር ሰላምና አንድነት መስፈን በጋራ ሊቆም እንደሚገባም ተመላክቷል።

የድጋፉ አስተባባሪ ኡስታዝ አል ነጋሽ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ድጋፉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ በማሰብ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማውን ህዝብ በማስተባበር በተገኝ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እርድ በማከናወን ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች የበዓል መዋያ ማዕድ ማጋራታቸውን ጠቁመዋል።

የተቸገሩ ወገኖች መድረስና ያለንን ማካፈል የእስልምና ሀይማኖት አስተምህሮ ነዉ ያሉት ደግሞ በከተማው የኑር መስጂድ ኢማም ሼህ መሀመድ አሚን አባድር ናቸው።

በተለይ የዘንድሮው መውሊድ ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.ዓ.ወ) ለመላው ዓለም የተላኩና የእሳቸውን ልህቀት በሚገልፅ መልኩ "የእዝነቱ ነቢይ" በሚል መሪ ቃል እየተከበረ መሆኑን ጠቅሰዋል።


ህዝበ ሙስሊሙ የነብዩ ሙሀመድን (ሰ.ዓ.ወ) ፈለግ በመከተል በዓሉን ሲያከብር ከጎኑ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።


በተለይ በበዓሉ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህልን ከማዳበር ባለፈ ለሀገር ሰላምና አንድነት መስፈን በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።


በዓሉን ስናከብር ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና የተጀመሩ ሀገራዊ የዕርቅና የሰላም መንገዶች እንዲሳኩ ዱዓ በማድረግ ጭምር ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።


የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑ ወገኖች መካከል ወይዘሮ ፈትያ ሁሴን አንዷ ሲሆኑ ድጋፉ የነብዩ መሃመድ (ሰ.ዓ.ወ) የመውሊድ በዓል በደስታ እንዲያሳልፉ ማድረጉን ጠቅሰው
ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም