የውሻ እብደት በሽታን እኤአ በ 2030 ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተተገበረ ነው

228

አዳማ መስከረም 28/2015... የውሻ እብደት በሽታን እኤአ በ2030 ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ተግባር መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

በኢትዮጵያ የውሻ እብደት በሽታያለበትን ሁኔታና እየተሰጠ ያለው ዘርፈ ብዙ ምላሽ ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላትና ዘርፎች የተሳተፉበት ውይይት በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ተወካይ አቶ ግርማ ሙሉጌታ እንደገለፁት የውሻ እብደት በሽታን ለመከላከልና ለማጥፋት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ስትራቴጂ ተነድፎ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

በዚህም በዘጠኝ ክልሎችና 13 ከተሞች ስለበሽታው ጉዳት ህብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ ከማዳበር ባለፈ 154 ሺህ 953 ውሾች ማስከተብ መቻሉን ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2030 ዓ.ምየውሻ እብደት በሽታን ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ግብ ተቀምጧል ያሉት አቶ ግርማ በዚህም በየዓመቱ በሀገሪቷ ካሉት ውሾች 70 በመቶ የማስከተብ ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

በሽታው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካና ኤሺያ ሀገራት ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱ በየዓመቱ ከ8 ነጥብ 6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በሽታውን ለማከም ወጪ እንደሚደረግ በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች  ያሳያሉ ብለዋል።

80 በመቶ የሚሆኑ ለበሽታው ተጋላጭ የሚሆነው በገጠር የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት ህፃናት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የውሻ እብደት በሽታ ተገቢውን ትኩረት ባለማግኘቱና በሽታውን ለመከላከል በቂ ሀብት ያለመመደብ፣ የህብረተሰቡ ግንዛቤ ያለመዳበርና የቅንጅታዊ ስራ ያለመኖር የመከላከሉ ስራ በሚፈለገው መልኩ እንዳይሰራ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።

በበሽታው የተያዙ ውሾች ንኪሻና ከውሾቹ በሚወጣው ፈሳሾች ንኪኪ ለበሽታው እንደሚያጋልጥ ጠቅሰው በሽታውን ለማጥፋት የተነደፈው ስትራቴጂ የታለመውን ግብ እንዲያሳካ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የተቀናጀ የጤና፣ የግብርናና ማህበራዊ ዘርፎች ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ህብረተሰብ ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ሲሳይ ጌታቸው እንደገለፁት በዘንድሮው ዓመት 250 ሺህ ውሾችን ለማስከተብ እየተሰራ ነው ብለዋል።

''ባለቤት የሌላቸው ውሾች መከታተልና ማስከተብ፤ ባለቤት ያላቸው ውሾችም እንዲከተቡ ማስቻል አለብን'' ያሉት ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ፣ መዘጋጃ ቤቶች፣ የጤናና ግብርና ዘርፎችን ጨምሮ የግብረሰናይ ድርጅቶችን ማሳተፍ አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

የውሻ እብደት በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ 59 ሺህ ሰዎች በየዓመቱ የሚሞቱ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ 2 ሺህ 700 ሰዎች በየዓመቱ ህይወታቸውን እንደሚያጡ ጥናቶችን መነሻ አድርገው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አብይ የጤና ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ፈይሳ ረጋሳ በበኩላቸው የውሻ እብደት በሽታ በኢትዮጵያ በብዛት የሚታዩት አደገኛ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።

ከአፋርና ሶማሌ ክልሎች ውጭ በሽታውን ለማጥፋት የሚያስችሉ ስራዎች በዘጠኝ ክልሎች በአሁኑ ወቅት እየተሰሩ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም