የፍትህ አገልግሎትን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ሚዛናዊ ለማድረግ በሳይንሳዊ አሰራሮች የመደገፍ ስራ ሊጠናከር ይገባል- ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ

110

መስከረም 27/2015 (ኢዜአ) የፍትህ አገልግሎትን ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ሚዛናዊ ለማድረግ በሳይንሳዊ አሰራሮች የመደገፍ ስራ መጠናከር እንዳለበት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሚቴዎስ ተናገሩ፡፡

በዚህ ዙሪያ ግንባታው ተከናውኖ ለስራ ዝግጁ የሆነው የሳይንስ ሙዚየም ለፍትህ ስርአቱ ዘመናዊነት ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

የሳይንስ ሙዚየም መስከረም 24 ቀን 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ መከፈቱ ይታወሳል፡፡

ሙዚየሙ ቋሚ እና ጊዜያዊ ዐውደ ርዕይ ማሳያ ቦታዎች ያሉት ሲሆን ከሙዚየሙ መከፈት ጋር ተያይዞም የተከፈተው አውደርዕይ በከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በመጎብኘት ላይ ነው።

በጉብኝቱ ላይ ያገኘናቸው የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፤ የሙዚየሙ መገንባት ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለችበትን ደረጃ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በጉብኝታቸውም የጤናውን ዘርፍ በማዘመን ህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚረዱ የቴክኖሎጂ ስራዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

በትምህርቱም ዘርፍ ትውልዱ ጥራት ያለው ትምህርት በማግኘት የአገሪቷን የወደፊት ተስፋ እውን ለማድረግ የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ስለመኖራቸው አስረድተዋል፡፡

በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋና ሚዛናዊ የፍትህ ስርአት ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት በሳይንሳዊ አሰራሮች የተደገፈ የፍትህ ስርአት ስለሚያስፈልግ የሙዚየሙ እውን መሆን ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቴክኖሎጂው ዘርፍ ራሱን ችሎ ለብቻው የሚታይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዘርፎች የስራ ክንውን ቀልጣፋ እንዲሆን የሚረዳ ወሳኝና ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይ ያገኘናቸው የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር በከር ሻሌ፤ የሳይንስ ሙዚየም እውን መሆኑ በቴክኖሎጂ የዳበረችና ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተመርቆ የተከፈተው የሳይንስ ሙዚየም በሰባት ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ሁለት ግዙፍና ዘመናዊ ህንፃዎችም አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም