በደብረታቦር ከተማ የመማሪያና የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች ተገነቡ

93

ባህር ዳር፤ መስከረም 27/2015 በደብረታቦር ከተማ ከ25 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የመማሪያና የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ዛሬ ተመረቁ።

 " ኤስ ኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች " በተባለው ድርጅት  የተገነቡት ፕሮጀክቶቹ  በተመረቁበት ወቅት በድርጅቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ እንዳሉት፤ ድርጅቱ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች በመሳተፍ መንግስትን እያገዘ   ይገኛል።

በዚህም ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትንና ወጣቶችን ተንከባክቦ ለቁም ነገር በማብቃት፣ በእናቶች ገቢ ማስገኛ ፣ በአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ፣ በትምህርት ተቋማት ግንባታና ሌሎች የልማት ስራዎች በመሰማራት ለውጤት እያበቃ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ  የተመረቁት ደግሞ ከ25 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ያስገነቧቸው የመማሪያና የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከግንባታዎቹ መካከል በከተማው የእናቲቱ ማርያምና የታቦር የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 16 ክፍሎች ያሏችው አራት ደረጃቸውን የጠበቁ ህንፃዎች ከነተጓዳኝ መገልገያዎች  ይገኙበታል።

እነዚህም  የተማሪ ክፍል ጥምርታውን በማሻሻል ጥረት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አስረድተዋል።

ሌላ ባለ ሁለት ወለል ያለው  የገቢ ማስገኛ ህንፃ ደግሞ 15 ሱቆች፣ ሬስቶራንት፤ ካፌና  የመሰብሰቢያ አዳራሽ አካቶ በኪይራይ በየወሩ እስከ 100 ሺህ ብር በማስገኘት በአካባቢ  አቅመ ደካሞች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተመልክቷል።

የደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ባሻ እንግዳው በበኩላቸው ፤ኤስኦኤስ በከተማ አስተዳደሩ ህብረተሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን እየተገበረ  እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለምረቃ የበቁት የመማሪያና የገቢ ማስገኛ ህንፃዎች በሁለት ዓመት ውስጥ  ተንገብተው መጠናቀቃቸውና ለሌሎች የልማት ፕሮጀክቶቻችን  ተሞክሮ ያስገኙ ናቸው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩም በተለይ ድርጅቱ የገቢ ማስገኛ ህንፃውን ለመገንባት ወደ ከተማው ሲመጣ 360 ካሬ ሜትር  ቦታ በነፃ ማስረከቡን ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ተወካይ አቶ ምስራቅ ተፈራ ፤ በክልሉ ከ300 በላይ ፕሮጀክቶች ለመተግበር ከ28 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል መድበው የሚያንቀሳቅሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ኤስኦኤስ የህፃናት መንደሮች በተለይም ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን  በማስተማርና አቅም የሌላቸው ቤተሰቦችን በገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች በማሳተፍ እያበርከተ ያለው አስተዋፅኦ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም