የሶማሌ ክልልን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ለማዋል እየተሰራ ነው – ቢሮው

153

ጅግጅጋ ፤ መስከረም 27/2015(ኢዜአ) በሶማሌ ክልል ያለውን እምቅ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የክህሎትና የስራ እድል ፈጠራ ቢሮ አስታወቀ።

በበጀት ዓመቱ ለ150 ሺህ  ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር  ታቅዷል።

የቢሮው ምክትል ሀላፊ ወይዘሮ ሂቦ አህመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት እንዲሁም  ከልማት ድርጅቶች  ጋር በመቀናጀት በክልሉ ያሉትን ሀብቶች  ለወጣቶች የስራ ማግኛ እንዲሆን እየተሰራ ነው፡፡

ለስራ እድል ማስገኛ ክልሉ ካሉት ሀብቶች መካከል  ሰፊ ለም መሬትና ውሃ ለከተማ ግብርና ፣ በአካባቢው  በስፋት እየተካሄዱ ያሉ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችና አገልግሎት ዘርፎች  እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ለስራው መሳካት ከመሬት ዝግጅት ሌላ ቀደም ሲል ከተገነቡ አምስት የማምረቻ እና የመሸጫ ሼዶች በተጨማሪ ዘንድሮ ዘጠኝ  ሼዶች እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡

ወጣቶቹ ያሉባቸውን የሙያ ክፍተቶች ለማስተካከል በክልሉ ከሚገኙ 13 የቴክኒክና የሙያ ኮሌጆች ጋር የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል  ወይዘሮ ሂቦ።

በማሀበር የተደራጁ ወጣቶች በሚያቀርቡአቸው አዋጪ የስራ ምክረ-ሀሳብ በባለሙያዎች እየተገመገመ ብድር እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል ለክልሉ ወጣቶች የተሰጠው 300 ሚሊዮን ተዘዋዋሪ ብድር በማስመለስ በአዲስ ወደ ስራ ለሚገቡ እንደሚተላለፍ ጠቅሰው፤ እስከአሁንም 70 ሚሊዮን ብር መመለሱን ጠቁመዋል ፡፡

ለወረዳዎችና ለከተማ አስተዳደሮች ከባንኮች ብድር መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለ150ሺ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር  የታቀደውን ለማሳካት ዘርፉን ከሚመሩት  ከከተሞችና ወረዳዎች አመራሮች  ጋር የስራ ውል ስምምነት መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡

የጅግጅጋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ አደን አብዲሰመድ እንዳሉት፤ ኮሌጁ በመደበኛ መረሀ-ግብር ከሚያስተምራቸው ተማሪዎች በተጨማሪ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች አጫጭር የሙያ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ ጥረት እያደረገ ነው፡፡

ዘንድሮም በኮንስትራክሽን፣በማኑፋክቸሪንግ፣በግብርና፣በኤሌትሪክ ስራ፣በአዋጪ የቢዝነስ ፈጠራ፣በሆቴልና ቱሪዝም መስኮች ከ1ሺ በላይ ወጣቶችን ለማሰልጠን መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በተጓዳኝም  በማሀበረሰብ ውስጥ ለጥቃቅንና አነስተኛ ስራ ላይ የሚስተዋለውን የተሳሳተ አመለካከት ለመቀየር የኮሌጁ ባለሙያዎች በተመረጡ የክልሉ ወረዳዎች ማህበረሰቡን እያወያዩ ናቸው ብለዋል፡፡

በጅግጅጋ በግል ቡሉኬት ማምረቻ ተቀጥሮ  በመስራት ላይ የሚገኙት ወጣት ጀማል ሀቢብ በሰጠው አስተያየት ከ10 ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት  የራሳቸውን ቡሉኬት ማምረቻ ለመክፈት እየተዘጋጁ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡

መንግስት ስልጠና፣ብድርና ቦታ ቢያመቻችላቸው በኑሮቸው መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ገልጿል።