የውጭ አገራት ገንዘቦችን በህገ-ወጥ የሃዋላ አገልግሎት ሲመነዝሩ የነበሩ 391 ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው እንዲዘጋ ተደረገ

326

መስከረም 27/2015 (ኢዜአ) የውጭ አገራት ገንዘቦችን በህገ-ወጥ የሃዋላ አገልግሎት ሲመነዝሩ የነበሩ 391 ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው እንዲዘጋ መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ የጥቁር ገበያ ቁጥጥርና አስተዳደራዊ እርምጃ፣ የዋጋ ግሽበትና ህገ-ወጥ የውጭ አገራት ገንዘብ ግብይትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ በመደረጉ ውጤት እየተመዘገ ቢሆንም የዋጋ ግሽበትና የንግድ ስርዓቱን ከማዘመን አንፃር ውስንነት እንዳለ ተናግረዋል።

በህገ-ወጥ መልኩ የሚከናወን የውጭ አገራት ገንዘብ ምንዛሬ ለዋጋ ግሽበትና ለንግድ ስርዓቱ  የራሱን አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬ ስራ በሚሰሩ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቁመው በጥቁር ገበያ የምንዛሬ ስራ ሲሰሩ የተደረሰባቸው 391 ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው እንዲዘጋ መደረጉን ተናግረዋል።

በወጀሉ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የግለሰቦችን ስም ዝርዝር ለፍትህ ሚኒስቴር በመላክ የምርመራ ስራው እንዲቀጥል መደረጉንም ጠቁመዋል።

እንዲህ አይነት ወንጀሎችን ለመከላከልና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ የተጠናከረ የቁጥጥር ስራ ይደረጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያንም በግለሰብ ደረጃ ከ100 ሺህ ብር በላይ ለድርጅቶች ደግሞ ከ200 ሺህ ብር በላይ በቤት ውስጥ ማስቀመጥ የተከለከለ መሆኑን መገንዘብ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

በመሆኑም በውጭ አገራት ገንዘብ ግብይት መፈጸምም ሆነ በህገ-ወጥ መንገድ ይዞ መገኘት እንደማይቻል ጠቅሰዋል።

በህገ-ወጥ መልኩ ወርቅ ቤት ውስጥ መከማቸት የማይቻል መሆኑን ገልጸዋል።