ባለፉት 2 ወራት ከወጪ ንግድ ከ61 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል -- ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

151

አርባ ምንጭ መስከረም 27/2015 (ኢዜአ) ባለፉት ሁለት ወራት ከወጪ ንግድ ከ61 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ  የ1ኛ ሩብ ዓመት ስራ አፈጻጸም ግምገማ በአርባ ምንጭአካሂዷል፡፡

የዕድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡልልታ ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋሙ በዋናነት የወጪና ተኪ ምርቶችን በጥራትና በመጠን ለማሳደግ እየሰራ ይገኛል ፡፡

በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ስኬታማ ማድረግ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸው ለዚህም የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ የማስፈጸም አቅም መፍጠር  ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግዱ 539 ሚሊየን ዶላር  ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በ1ኛው ሩብ ዓመት ከታቀደዉ የ70 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር በሁለት ወራት ውስጥ 87 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ለአምራች ኢንዱስትሪው ሌላው ግቡ የስራ ዕድል መፍጠር በመሆኑ በ2015 ዓ.ም 369 ሺህ የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ነው የጠቀሱት።

ከዚህም ባለፉት ሁለት ወራት ለ28 ሺህ ዜጎች በዘርፉ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን በማከል።

ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ፣ ተወዳዳሪነት ለማሳደግና መዋቅራዊ ሽግግርን ለማሳለጥ ዓላማ ያደረገ “የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በርካታ ለውጦች እንዲመዘገቡ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ  139 ስራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው በዋቢነት አስታውሰዋል፡፡

ጨርቃ ጨርቅ፣ ምግብና መጠጥ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ኬሚካልና ኮንስትራክሽን እንዲሁም ብረታ ብረትና ሌሎች ምርቶች በተጠቀሰው ጊዜ ወደ ውጭ የተላኩ ምርቶች መሆኑን በሚኒስቴሩ የወጪ ምርቶች መር ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘርሁን አበበናቸው።

ከእነዚህ ውስጥ ጨርቃ ጨርቅ፣ ምግብና መጠጥ ሰፊ ድርሻ እንደሚይዙ በግለጽ "በአጠቃላይ 61 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ኤክስፖርት ተደርጓል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም