ባህርዳር 10ኛውን የጣና ፎረም ጉባኤ ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች -መምሪያው

164

ባህር ዳር፤ መስከረም 26 ቀን 2015(ኢዜአ) ባህር ዳር 10ኛውን ዙር የጣና ፎረም ጉባኤ በተሳካ መንገድ ለማስተናገድ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራ ማጠናቀቋን የከተማው አስተዳደር ገለጸ።

የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ በትግሉ ተስፋሁን ለኢዜአ እንዳሉት ታላላቅ መሪዎች የሚገኙበትንና በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ዙሪያ የሚመክረውን የጣና ፎረም በተሳካ መንገድ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ለዚህም ከከተማ አስተዳደሩ የሚጠበቁ የሰላምና ደህንነት ስራዎችና ኢትዮጵያዊ መስተንግዶን በተላበሰ አግባብ እንግዶች እንዲስተናገዱ የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

የተላላቅ መሪዎች ፎረም በአፍሪካ ደህንነት ዙሪያ (Tana high level forum on security in Africa) በሚል መሪ ሐሳብ ለ10ኛ ጊዜ ለሚካሄደው ፎረም ስኬት የቅድመ ዝግጅት ስራውን የሚያስተባብር ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል ብለዋል።

በአፍሪካ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሄ ለማፈላለግ የተቋቋመውና በአፍሪካ ኢኮኖሚ፣ ሰላም፣ ንግድ ትስስርና የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ዙሪያ የሚመክረው ፎረሙ በስኬት እንዲከናወን በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ተሳታፊ እንግዶች የሚያርፉባቸው ሆቴሎችን የማመቻቸት ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ሆቴሎችም የእንግዶቹን ደረጃ የሚመጥን መስተንግዶ እንዲያቀርቡ ምክክር መደረጉን አመልክተዋል።

የመድረኩ ባለቤት የሆነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቢሆኑም ከተማው ከመድረክ መለስ ባሉት ጉዳዮች የዝግጅት ስራዎችን እያጠናቀቀች ነው ብለዋል።

ፎረሙ በዚህ ወቅት መካሄዱ በኮረና ቫይረስና አሸባሪው የህወሓት ቡድን በከፈተው ጦርነት ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ፍሰት መልሶ ለማነቃቃትና በተለይም በውጭ ዜጎች ላይ ያለውን አመለካከት ለማስተካከል ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነም አክለዋል።

እንዲሁም ባህር ዳር ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ሰላሟ የተረጋገጠና ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ መሆኗን እንግዶቹ እንዲያውቁ እድል የሚፈጥር መሆኑንም አመልክተዋል።

መድረኩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የከተማዋ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመሆን የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል ሃላፊው።

የጣና ፎረም ከጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን ከተለያዩ ሃገራት የተውጣጡ የሀገራት መሪዎች፣ አምባሳደሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም