በኢትዮጵያ በሙከራ ደረጃ ያለው ቆሻሻ ውሃን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራ በስፋት ሊተገበር ይገባል- የዘርፉ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በሙከራ ደረጃ ያለው ቆሻሻ ውሃን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራ በስፋት ሊተገበር ይገባል- የዘርፉ ምሁራን
መስከረም 26/2015 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ በሙከራ ደረጃ ላይ ያለው ቆሻሻ ውሃን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራ በስፋት ሊተገበር እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
የከተሞችን የፍሳሽ አወጋገድ ማሻሻልን በተመለከተ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከተለያዩ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የከተማ ውሃ አገልግሎቶች፣ በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ለጋሽ አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ እና በጅማ ዩኒቨርሲቲ የውሃና የአካባቢ ምህንድስና ፕሮፌሰር ዶክተር ኢንጅነር ኢሳያስ አለማየሁ፤ ቆሻሻ ውሃን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ሂደት ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ አገሮች እምብዛም አለመሰራቱን ይናገራሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥሩ ጅምሮች መታየታቸውን አስታውሰው ከአፍሪካ በተለይም ጋና እና ደቡብ አፍሪካ መልካም ተሞክሮ አላቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያም በሙከራ ደረጃ ላይ ያሉ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመው በዚህ ዘርፍ በዩኒቨርሲቲዎች በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎች አሉ ብለዋል።
በተለይም በከተሞች ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ስራዎችን በማጠናከር ቆሻሻ ውሃን በማከም ለመልሶ ጥቅም ማዋል ላይ ብዙ ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህም መንግስት፣ በዘርፉ የሚሰሩ ተቋማት፣ የግል ሴክተሩ እና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ተሳትፎና ትብብር ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የአፍሪካ የውሃ ልህቀት ማዕከል ሃላፊ ዶክተር ዘለቀ ዘውገ በበኩላቸው፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ቆሻሻ ውሃን በማጣራት ለመልሶ ጥቅም ማዘጋጀት ላይ በስፋት መሰራት አለበት ሲሉም መክረዋል።
በዚህ ዘርፍ የትምህርት ተቋማት ጥናትና ምርምሮችን በመስራት ለስራው ስኬት የድርሻቸውን መወጣት አለባቸውም ብለዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር አስፋው ዴንጋሞ በበኩላቸው፤ በከተሞች ያለውን የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓት በማዘመን ቆሻሻ ውሃን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ስራ በልዩ ትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።
በሙከራ ደረጃ በተለያዩ ከተሞች የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመው በቀጣይ ዓመታት ስራውን የማስፋት እቅድ መኖሩንም ጠቁመዋል።
በተለይ በመጠጥ ውሃ ብቻ ላይ ትኩረት ያደረገውን የህግ ማዕቀፍ በማሻሻል በፍሳሽ ማስወገድ ላይም ለመስራት መታቀዱን ተናግረዋል።