የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የሚያስቃኝ አውደ-ርዕይ በእንጦጦ ፓርክ ተከፈተ

91

መስከረም 26 ቀን 2015 (ኢዜአ)የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የሚያስቃኝ አውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ እንጦጦ ፓርክ ውስጥ ተከፈተ።

አውደ ርዕዩን የቱሪዝም ሚኒስቴር፣የፈረንሳይ መንግሥት እንዲሁም የቅዱስ ላልይበላ ደብር ጽህፈት ቤት በጋራ አዘጋጅተውታል።

በአውደ ርዕዩም የአብያተ ክርስቲያናቱን ሙሉ ታሪክ በፎቶና ቨርቹዋል በተሰኘ ቴክኖሎጂ ለዕይታ ቀርቧል።

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እና በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ አውደ ርዕዩን በጋራ መርቀው ከፍተውታል።

አውደ ርዕዩ ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ የተገለጸ ሲሆን ይህም ጎብኚዎች በአካል በመገኘት የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እንዲጎበኙ መነሳሳት እንደሚፈጥርም ታምኖበታል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ አውደ-ርዕዩን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት አውደ ርዕዩ ዲጂታል አውደ ርዕይ በመሆኑ በአይነቱ የመጀመሪያ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን በቴክኖሎጂ ማስተዋወቅ ላይ ዕቅድ የተያዘ ሲሆን ዛሬ የተከፈተው ቨርቹዋል ሪያሊቲ አውደ-ርዕይ የዕቅዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

የፈረንሳይ መንግስት ባለፉት ሶስት አመታት አብያተ ክርስቲያናቱን ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ሲደግፍ መቆየቱን አንስተዋል።

ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን ለመጠገን በፈረንሳይ መንግስት ድጋፍ ጥናት እየተካሄ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

አውደ-ርዕዩ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በላልይበላ ከተማና ከኢትዮጵያ ውጭም ለዕይታ እንደሚበቃ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም