የግብዓት እጥረትና በቂ የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት አለመኖር በስራችን ላይ እክል ፈጥሯል- የአንጎልና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና ባለሙያዎች

160
አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 የግብዓት እጥረትና በቂ የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት አለመኖር በአንጎልና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ህክምና አገልግሎት ላይ እክል መፍጠሩን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለፁ። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የግብዓት ችግሮችን ለመፈታት የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁሞ፤ ባልተቀናጀ መልኩ የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በኤጀንሲ ደረጃ ለማደራጀት መመሪያ ማውጣቱን አስታውቋል። በኢትዮጵያ የአንጎልና የህብለ ሰረሰር ቀዶ ጥገና ህክምና በአመዛኙ ከውጭ አገራት በሚመጡ የጤና ባለሙያ ቡድኖች ላይ ጥገኛ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአገር ውስጥ የዘርፉን ባለሙያ ማሰልጠን ከተጀመረበት 12 ዓመታት ወዲህ ግን ህክምናው በዋናነት በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ኢዜአ ያነጋገራቸው ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ መንግስት በዘረፉ ኢትዮጵውያን ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ መልካም ጅምር እያሳየ ቢሆንም አገልግሎቱን በተደራጀ መልኩ ለመስጠት የሚያስችሉ ግብዓቶችን ማሟላት ላይ ግን አሁንም ድክመት ይሰተዋላል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የነርቭ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ዶክተር አቤንዘር ትርሲት ከዚህ በፊት በዘርፉ የነበረው ዋነኛ ማነቆ የባለሙያ እጥረት ነበር ይላሉ። በመላው ኢትዮጵያ ከአስር ዓመታት በፊት የነበሩ የነርቭ ቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቶች ከሁለት እንደማይበልጡ አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን በዘርፉ ስፔሻላይዝ ያደረጉ 26 ባለሙያዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጡ  ይገኛሉ  ብለዋል፡፡ በሆስፒታሉ በሚገኘው የህክምና ትምህርት ቤትም 44 ባለሙያዎች እየሰለጠኑ መሆኑን አክለዋል፡፡ የህክምና ቁሳቁሶችን ማሟላት ላይ ግን ሰፊ ክፍተት እንዳለ ነው ዶክተር አቤኔዘር የሚናሩት፡፡ ከአደጋ ጋር ተያይዞ ተጎጂዎችን ወደ ሆስፒታል የማጓጓዙ ሂደትም በተቀናጀ መልኩ እየተሰጠ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው የትራፊክ አደጋ ጋር ተያይዞ የነርቭ ቀዶ ጥገና የሚስፈልጋቸው ተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በዘውዲቱ ሆስፒታል የአዕምሮና ህብለ ሰረሰር ቀዶ ጥገና ስፒሻሊስቱ ዶክተር ታደሰ ከበደ ናቸው፡፡ በህክምና ቁሳቁስ እጥረቱም በቀላሉ መዳን የሚችሉ ተጎጂዎችን  ለመታደግ  እክል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡ በጤና ጥበቃ ሚንስቴር የድንገተኛ ህክምና ዳይሬክቶሬት የአደጋ ህክምና አስተባባሪ ሲስተር ቤተልሄም ሽፈራው በበኩላቸው እጥረቱ መኖሩን አምነው፤ ሚኒስቴሩ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ ችግሩን ለመቅረፍ  እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አገር ውስጥ መመረት የሚችሉትን ግብዓቶች ከብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖርሽን ጋር በመቀናጀት ለማምረት ስራ መጀመሩንም አክለዋል፡፡ ባልተቀናጀ መልኩ የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን በኤጀንሲ ደረጃ ለማደራጀት መመሪያ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ አንድ ብሔራዊ የድንገተኛ ጥሪ ማዕከል ለማበጀት ከተለያዩ ባለድርሻ  አካላትጋር በመሆን እየሰራ መሆኑንም አውስተዋል፡፡                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም