የተፈጥሮ ማዳበሪያን ጨምሮ የግብርና ግብዓቶችን ተደራሽ በማድረግ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

168

ጎባ፣መስከረም 26/2015 (ኢዜአ) የተፈጥሮ ማዳበሪያን ጨምሮ የግብርና ግብዓቶችን በስፋት ተደራሽ በማድረግ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑ የባሌ ዞን አስታወቀ።

በባሌ ዞን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና በፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሮቤ ከተማ ተካሂዷል።

የምክክር መድረኩ የተዘጋጀው በሁለቱ የባሌ ዞኖች የግብርና ጽህፈት ቤቶችና 'ኢኮ ግሪን' የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ድርጅት ጋር መሆኑ ታውቋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የባሌ ዞን የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልይ መሀመድ እንዳሉት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

በተለይም የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የግብርና ጎብዓቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም የተፈጥሮ ማዳበሪያ የመሬት ለምነትን በማሻሻል ቀጣይነት ያለው ምርታማነት ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ ያደርጋል ነው ያሉት።

ከዚህም አልፎ ዘንድሮ ከውጪ ይገባ የነበረውን የስንዴ ምርትን በማስቀረት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጪ ለመላክ የተያዘው ዕቅድ በማሳከት ረገድ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል።

በዞኑ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ከ180 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የግብርና ግብዓቶችን በመጠቀም በመኽር ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘሮች እየለሙ መሆኑን አንስተዋል።

የ'ኢኮ ግሪን' ፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ድርጅት ምክትል ዳይሬክተር አቶ የኋላሸት ጌታሁን በበኩላቸው ድርጅታቸው አርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነቱን በማሳደግ በምግብ እራሱን ከመቻል አልፎ ገበያን ማዕከል አድርጎ እንዲያመርት ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያው በየአካባቢው የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን በግብዓትነት የሚጠቀም በመሆኑ አርሶ አደሩ ምርታማነትን ከመጨመር በተጓዳኝ ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ የሚያወጣውን ወጪ ይቀንሳል ነው ያሉት።

የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም ልምድ ካላቸው የዞኑ ሲናና ወረዳ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች መካከል የቦ መሐመድ እንዳሉት ፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያው ምርታማነት እንዲያድግ አግዟቸዋል።

''ለአፈር ማዳበሪያ የምናወጣውን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ቀጣይነት ያለው ግብርና ለማካሄድ እገዛ ያደርጋል'' ነው ያሉት።  

ሌላው አርሶ አደር ኡስማን በከር በበኩላቸው የተፈጥሮ ማዳበሪያው የአፈር ለምነትን የሚጨምር መሆኑን ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።

በባሌ ዞን በ2014/15 የመኽር የምርት ወቅት ከ240 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ የሰብል ዘሮች መሸፈኑን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኛው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም