በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅቱ የለማ ሰሊጥ እየተሰበሰበ መሆኑ ተገለፀ

244

መተማ መስከረም 26/2015 (ኢዜአ) --- በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅቱ በ120 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰሊጥ የጥራት ደረጃውን በጠበቀ አግባብ የመሰብስብ ሥራ መጀመሩን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ጌትነት ካሳሁን እንደተናገሩት በዞኑ በዚህ የመኽር ወቅት የለማውን ሰሊጥ ብክነት ሳይደርስበት ለመሰብሰብ ርብርብ እየተደረገ ነው።

የሰሊጥ ሰብል እንደ ሌሎች ሰብሎች በስብሰባ ወቅት ጊዜ የማይሰጥና በወቅቱ መሰብሰብ ካልተቻለም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደመሬት የሚፈስ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም የደረሰውን ሰሊጥ ከ200 ሺህ በላይ የሰው ሃይል በማሰማራት የመሰብሰብ ሥራ የተጀመረ ሲሆን እስካሁንም ከ10 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የለማውን መሰብሰቡን ተናግረዋል።

የሰሊጥ ምርት ስብሰባውን እስከ ጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በሰሊጥ ከለማው መሬትም ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት አቶ ጌትነት፣ "የምርት ብክነት እንዳይገጥም በጥንቃቄ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

"ታጭዶ የቆመ ሰሊጥ በእንስስሳት፣ በነፋስና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ምክንያት ለብልሽት እንዳይጋለጥ ለማድረግም ከአጨዳ ጎን ለጎን አራግፎ ወደኩንታል የማስገባት ሥራ እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ቡድን መሪው እንዳሉት ሰሊጡ በ400 ባለሃብቶችና 40 ሺህ በሚጠጉ አርሶ አደሮች የለማ ሲሆን፤ ምርቱም ለውጭ ገበያና ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርብ ነው።

በሰሊጥ ልማት ኢንቨስትመንት የተሰማራው አበበ ውለታው እርሻ ልማት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ውለታው በበኩላቸው ከ60 ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ ማልማታቸውን ገልጸዋል።

የሰሊጥ ሰብሉ በመድረሱ ከ400 በላይ የጉልበት ሠራተኞችን በመጠቀም እየሰበሰቡ መሆኑንና እስካሁንም በ10 ሄክታር የለማው ሰሊጥ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ከአጨዳ ሥራ ጎን ለጎን የማራገፍ ሥራ ለማከናወን ተጨማሪ የሰው ሃይል እንደሚጠቀሙ ገልጸው፤ ከለማው መሬት ከ300 ኩንታል በላይ የሰሊጥ ምርጥ እንደሚጠበቁ ተናግረዋል።

ሌላኛው በመተማ ወረዳ የኩመር አፍጥጥ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይርጋ ጥላሁን በበኩላቸው፣ በሰሊጥ ከሸፈኑት 3 ሄክታር መሬት ውስጥ ግማሽ ሄክታር የሚሆነውን መሰብሰባቸውን ገልጸዋል።

"በቀጣይ ሁለት ሳምንታትየጉልበት ሠራተኞችን በመጠቀም ምርቱን ሙሉ በሙሉ ለመሰብሰብ አቅጃለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።

በሰሊጥ ካለሙት መሬት 20 ኩንታል የሚጠጋ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅት ከአጨዳ ሥራው ጎን ለጎን የታጨደውን ሰሊጥ በማራገፍ እያስገቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በክረምቱ የመኽር ወቅት በዞኑ ከ449 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች የለማ ሲሆን ከ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም