የኩታገጠም እርሻ በአርሶ አደሩ ላይ የሚደርሰውን የተናጥል ጫና በማስቀረት በጋራ የመልማት ባህል እንዲጎለብት አድርጓል

160

መስከረም 25/2015 (ኢዜአ) በጉራጌ ዞን ምስራቅ መስቃን ወረዳ የኩታገጠም እርሻ መለመዱ በአርሶ አደሩ ላይ የሚደርሰውን የተናጥል ጫና በማስቀረት በጋራ የመልማት ባህል እንዲጎለብት ማድረጉን የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተጠቁሟል።

በዞኑ የምስራቅ መስቃን ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሻፊ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት አለው።

የሜካናይዝድ ቴክኖሎጂን አርሶ አደሩ መጠቀም መጀመሩ ቀደም ሲል የነበረበትን ድካም ከማስቀረት ጀምሮ ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

በኩታ ገጠም ማልማት በወረዳው አርሶ አደሮች ዘንድ እየተለመደ መምጣቱን ጠቁመው፤ የክላስተር እርሻ በጋራ ለመስራት ሰፊ ዕድል በመፍጠሩ የአርሶ አደሩ የተናጠል ጫና እየቀነሰ መሆኑን አመልክተዋል።

የወረዳው አስተዳደር ግብዓት ማቅረብን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተወሰኑ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ የጀመረው ወረዳው ዘንድሮ ከወዲሁ አቅዶ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ሻፊ ጠቁመዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ዕቅዱ በወረዳው ያለውን የውሃ አማራጭ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ አርሶ አደሩ የሶላር ሃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ፓምፕን ጨምሮ እንዲጠቀም የሚያስችል ዝግጅት መኖሩን ተናግረዋል።

የመኸር ሰብል ተሰብስቦ እንዳበቃም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የአካባቢው አርሶ አደሮች ከነበረው ልማዳዊ የእርሻ ስራ ተላቀው በሜካናይዝድ ቴክኖሎጂ ማልማት መጀመራቸው ውጤት እያስገኘላቸው መሆኑን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አመልክተዋል።

በተለይ በኩታ ገጠም ዘዴ ሰብል ማልማታቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳስገኘላቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም