የመንገድ ግንባታ ወሰን ማስከበርን በወቅቱ ማጠናቀቅ አለመቻል ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳት አያስከተለ ነው ተባለ

153
አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ግንባታ ወሰን ማስከበር ሥራ በወቅቱ አለመጠናቀቁ ፕሮጀክቶቹን በማጓተት ለምጣኔ ኃብታዊ ጉዳት መዳረጉን የከተማው መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ። በአዲሰ አበባ በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ከሚገኙ ከ100 በላይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል በርካቶቹ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ በገጠማቸው ችግር ሳቢያ ሥራቸው እየተጓተተ ነው። የካሳ ክፍያ ተፈጽሞላቸው ያልተነሱ የልማት ተነሺዎች፣ የቅርስ ቤቶች ያረፉባቸው አካባቢዎች እና የፍርድ ቤት እግድ የተላለፈባቸው ቦታዎች ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ዋነኛው ችግር የሚስተዋልባቸው ናቸው። ባለስልጣኑ በወሰን ማስከበር ሥራ ሂደት ያጋጠሙ ዋና ዋና ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ምክክር አካሂዷል። በከተማው እንዲተገበሩ ከተያዙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ  የሚያጋጥሙ የወሰን ማስከበሮችን በወቅቱ መፈጸም አለመቻሉ የከተማ አስተዳደሩን ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረግ ባሻገር የነዋሪውን የእለት ተለት እንቅስቃሴን በማደናቀፍ ላይ መሆኑም ተገልጿል። ለዚህ ደግሞ መሰረታዊው ምክንያት በሚመለከታቸው ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች መካከል ተቀናጅቶ ያለመስራት ክፍተት ነው ተብሏል። በዚህም ሳቢያ የመንገድ ሥራ ተቋራጮች ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ በሚፈጠርባቸው ፍራቻ ብቻ ከፍተኛ የግንባታ ጨረታ ዋጋ ያቀርባሉ፤ የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜንም ያራዝማሉ። ከዚህም ሌላ የወሰን ማስከበሩ በጊዜው ባለመጠናቀቁ የተነሳ ተቋራጮች በግንባታው መዘግየት ደረሶብናል ለሚሉት ኪሳራ ካሳና ሌሎች ጥያቄዎችን በማቅረብ መንግስትን  ለአላስፈላጊ ወጪ እየዳረጉት መሆኑም ተጠቁሟል። በባለስልጣኑ የወሰን ማስከበር ዳይሬክተር አቶ አንዳርጌ ፈታው በዚህ ወቅት እንደገለፁት፣ ለመንገድ ግንባታ መጓተት የወሰን ማስከበር ችግሮች   ዋነኛ ምክንያት ናቸው። በዚህ ረገድ ዋነኛ የሚባሉት የካሳ ክፍያ ተፈጽሞላቸው ያልተነሱ የልማት ተነሺዎች፣ የቅርስ ቤቶች ያረፉባቸው አካባቢዎች እና የፍርድ ቤት እግድ የተላለፈባቸው ቦታዎች ናቸው። የወሰን ማስከበር ችግሮቹ በከተማው በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተስተዋሉ በመሆኑ ይህንን ችግር ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መደረጉ መፍትሄ ለማምጣት ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ገልፀዋል። በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ መንገዶችና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢንጅነር ሰለሞን ኪዳኔ በበኩላቸው፤ለተፈጠሩት የወሰን ማስከበር ችግሮች ምንጭ በዋናነት የአመራር ክፍተት መሆኑን ገልፀዋል። በመሆኑም የወሰን ማስከበር ችግሮቹን ለመፍታት ከክፍለ ከተማ እስከ ከተማ ድረስ የተሾሙ አዳዲስ አመራሮች በመናበብና በቁርጠኝነት ጥብቅ የክትትልና የድጋፍ ሥርዓት በመዘርጋት  ችግሩን መፍታት አለባቸው ብለዋል። በአዲሱ በጀት ዓመት በአሁኑ ወቅት ያልተጠናቀቁ የወሰን ማስከበር ሥራዎች እስከ ጥቅምት መጨረሻ እንዲጠናቀቁ ይደረጋል። በዚህ ረገድ ህብረተሰቡም ዕቅዶቹን ቀድሞ እንዲያውቃቸው ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ወሳኝ መሆኑን  ዶክተር ኢንጅነር ሰለሞን አስገንዝበዋል። በአመራሩ ላይ ተጠያቂነት ያለበት ስርዓት መፍጠርም ችግሩ ለማቃለል እንደሚያግዝ ተናግረዋል። በተያዘው በጀት ዓመት በወሰን ማስከበር ሥራ ላይ ትኩረት የተሰጣቸው 65 ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ታቅዷል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም