ከምርምር ማዕከሉ የወጡ የሰሊጥና ዳጉሳ ዝርያዎች የተሻለ ምርት እንድናገኝ አስችለውናል -አርሶ አደሮች

247

ሰቆጣ ኢዜአ መስከረም 25/2015 ''ከሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከል '' የወጡ የሰሊጥና ዳጉሳ ዝርያዎች መጠቀማችን የተሻለ ምርት እንድናገኝ አስችሎናል'' ሲሉ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የዝቋላ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።

በዝቋላ ወረዳ የቀበሌ 01 ነዋሪ አርሶ አደር ጣምተው ቸኮለ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ባላቸው በግማሽ ሄክታር መሬት በልማዳዊ አስተራረስ ዘዴ በሚያርሱበት ወቅት ከሚያለሙት መሬት ከሁለት ኩንታል ያልበለጠ ምርት ያገኙ እንደነበር አስታውሰዋል።

ካለፈው አመት ጀምሮ ከሰቆጣ ዝናብ አጠር ግብርና ምርምር ማዕከሉ የወጡ "ሰቲት" የተሰኘ የሰሊጥ ዝርያና "ቆላ-1 እንቁ'' የዳጉሳ ዝርያ እንደቀረበላቸው ገልፀዋል።

በባለፈው የመኽር ወቅት የቀረበላቸውን "ቆላ-1'' እንቁ ዳጉሳ በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ ዘርተው ከስድስት ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በዘንድሮ መኽር እርሻም "ሰቲት" የተሰኘውን የሰሊጥ ዝርያን በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ዘርተው ማልማታቸውን ጠቁመው ካለሙት መሬት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ አመላክተዋል።

በወረዳው የቀበሌ 02  ነዋሪ አርሶ አደር ቄስ ተሻለ ወልደ ሩፋኤል በበኩላቸው ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ የቀረበላቸውን "ቆላ-1'' እንቁ የተሰኘ የዳጉሳ ዝርያን መጠቀም ጀምረዋል።

በባለፈው መኽር እርሻ ከአንድ ሄክታር ተኩል ማሳቸው ላይ ከዘጠኝ ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን አስታውሰው፤ በዘንድሮው መኽር እርሻም የእንቁ ዳጉሳ ዘር ዘርተው እያለሙ መሆናቸውን ገልፀዋል።


ምርጥ ዘርና ማዳበሪያን በመጠቀም በኩታ ገጠም እያለሙ የእንቁ ዳጉሳ ሰብል በመልካም ቁመና ላይ በመሆኑ ከባለፈው አመት የተሻለ ምርት እንደሚያገኙ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል ።

'ከምርምር ማዕከሉ የወጡና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ተስማሚና ፈጥነው የሚደርሱ የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ ነው'' ያሉት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ ናቸው።

ከምርምር ማዕከሉ የወጡ ሰሊጥ፣ እንቁ ዳጉሳና ማሾ ሰብሎች በ300 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም አስተራረስ መልማቱን ተናግረዋል።

ከምርምር ማዕከሉ የሚቀርቡ ምርጥ ዘሮችን በስፋት ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ መምሪያው መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የምርምር ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነ ባህሩ በበኩላቸው እንዳሉት ማዕከሉ ለደጋና ቆላማ አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እየቀረበ ነው።

ማዕከሉ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ወሎ ላስታ ወረዳ ባሉ አምስት ወረዳዎች 816 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ስድስት የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ማቅረብ መቻሉን አመልክተዋል።

በዝቋላ ወረዳ በ33 ሄክታር መሬት ላይ የእንቁ ዳጉሳና የሰሊጥ ምርጥ ዘሮችን በማባዛት ለአርሶ አደሮች በማቅረብ እንዲለማ መደረጉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በቆላማ አካባቢዎች ''ቆላ-1'' የተሰኘ እንቁ ዳጉሳ የሰብል ዝርያ በአነስተኛ የዝናብ ስርጭት ቶሎ የሚደርስ በመሆኑ አርሶ አደሩ በስፋት እየተጠቀመው መሆኑን ተናግረዋል።

የምርምር ማዕከሉ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ሌሎች የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን በስፋት ለማቅረብ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም