የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ኢንኮሞኮ ከተባለ ድርጅት ጋር በሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ተስማማ

110

አዲስ አበባ መስከረም 25/2015 (ኢዜአ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በቢዝነስ ሥልጠናዎችና የማማከር አገልግሎት በመስጠት ከሚታወቀው (ኢንኮሞኮ) ከተባለ ድርጅት ጋር በሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ስምምነት መፈጸሙን አስታወቀ።

የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በደረሱት ስምምነት መሰረት በሥራ እድል ፈጠራ ዙሪያ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ኢንኮሞኮ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በተለይም ስደተኞችን በማቋቋም በኩል ለሚደረጉ ጥረቶች እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የድርጅቱ አብይ ትኩረት ስደተኞች ላይ ቢሆንም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የእድሉ ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በሥራ ፈጠራና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ የሚያመቻች መሆኑንም ተናግረዋል።

ለኢንተርፕራይዞች ምስረታ አስፈላጊና መነሻ የሚሆናቸውን ገንዘብ የሚያቀርብ መሆኑን የገለጹት አቶ ንጉሱ ወደ ምርትና አገልግሎት በመሸጋገር የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ አጋዥ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢንኮሞኮ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጁሊያን ኦይለር ድርጅታቸው ከአሥር ዓመት በፊት በሩዋንዳ ሥራውን መጀመሩን ጠቅሰው፤ በሌሎች ሀገሮችም እያሰፋ መሆኑን ነው የገለጹት።

በምስራቅ አፍሪካ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በማማከር፣ በማሰልጠንና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

እ.ኤ.አ እስከ 2030 ኢትዮጵያን ጨምሮ በስምንት የአፍሪካ አገራት በ21 ቢሊዮን ዶላር ግማሽ ሚሊዮን ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ ስትራቴጂ ቀርጾ እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚሁ ድጋፍ ማዕቀፍ ውስጥም በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢንተርፕራይዞችን ተጠቃሚ እናደርጋለን ብለዋል።

ከዚህ በፊት በጅግጅጋ፣ አዲስ አበባ እና አሶሳ 650 ስደተኞችና የአካባቢውን ነዋሪዎች አሰልጥኖ ማስመረቁ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም