በክልሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቂቂያ ፈተና አሰጣጥ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል

206

ሚዛን አማን መስከረም 25/ 2015 (ኢዜአ) በክልሉ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና አሰጣጥ ሂደት በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ነቢዩ ኢሳይያስ እንደገለጹት የብሄራዊ ፈተና አሰጣጥ ሂደት በሰላማዊ እንዲካሄድ ፖሊስ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮችና ለሌች የፀጥታ አካላት ጋር በመዘጋጀት በቅንጅት ወደ ሥራ ገብቷል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከሚገኙ 152 ትምህርት ቤቶች ተፈታኞችን ወደመፈተኛ ዩኒቨርሲቲዎች እስኪደርሱ ደህንነታቸው እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ፈተናው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የፖሊስ ሚናና ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንደ ሀገር በትምህርት ሚኒስቴር በፈተናው ዙሪያ የወጡ ህጎችን ለማስከበር የክልሉ ፖሊስ ተልዕኮውን በአግባቡ እንደሚወጣም አስታውቀዋል።

ወላጆች፣ ተፈታኝ ተማሪዎችና መላው የክልሉ ህዝብ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት በአግባቡ በመፈጸም የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ኮሚሽነሩ መልዕክት አስተላልፈዋል ።

የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ መልቀቂያ ፈተና አሰጣጥ ከመስከረም 30 ጀምሮ በዩኒቨርሲቲዎች እንደሚሰጥ ቀደም ብሎ በሀገር አቀፍ ደረጃ መገለጹ ይታወሳል።