"ግድቤን በደጄ" የዝናብ ውሃን የማጠራቀም ፕሮጀክት ሥራ በይፋ ተጀመረ

204

መስከረም 25 /2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ ተጎጂ በሆኑ አካባቢዎች የሚተገበረው"ግድቤን በደጄ" የዝናብ ውሃን የማጠራቀም ፕሮጀክት ሥራ መጀመሩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ ተናገሩ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቦረና ዞን ተግባራዊ መደረግ የጀመረውን ከጣሪያ ላይ ውሃ የማሰባሰብና ጥቅም ላይ የማዋል ፕሮጀክት ጎብኝተዋል፡፡

"ግድቤን በደጄ" (ዳም አት ማይ ያርድ) በሚል መርህ በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሙከራ (ፓይለት) ፕሮጀክት ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል።

ከዚህ ተሞክሮ በመነሳትም በተደጋጋሚ በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ አካባቢዎች ይኸው ፕሮጀክት በይፋ መተግበር መጀመሩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ፤ "ግድቤን በደጄ" የዝናብ ውሃን የማጠራቀም ፕሮጀክት በቦረና ዞን በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና መንደሮች በመተግበር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ከጣሪያ ላይ የዝናብ ውሃን በማሰባሰብ በዘመናዊ መንገድ ወደ ተገነባ ገንዳ በማጠራቀም ንጽህናው በተጠበቀ መልኩ በአነስተኛ ማሽን በማውጣት ሕብረተሰቡ እንዲጠቀም ይደረጋል ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ በቦረና ዞን ስምንት ትምህርት ቤቶችና ለአንድ አካባቢ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ በተለይ በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ አካባቢዎች ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በዝናብ አጠር አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ መደረጉ ተማሪዎች በውሃ እጦት ትምህርት እንዳያቋርጡ ያግዛል ብለዋል።

በቀጣይ የውሃ እጥረት ባለባቸውና በተደጋጋሚ በድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የፕሮጀክቱ ትግበራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል።

በቦረና ዞን የተገነቡት የውሃ ገንዳዎች ከ120 ሺህ እስከ 200 ሺህ ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም እንዳላቸው ገልጸው፤ አንድ ጊዜ በሚይዙት ውሃ ከስድስት ወር በላይ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በቦረና ዞን ተግባራዊ የተደረገው ፕሮጀክት ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ለወደፊት ሕብረተሰቡ ጉድጓዶቹን በራሱ ጉልበት እንዲቆፍርና ሌሎች አነስተኛ ቁሳቁሶችን እንዲያሟላ ከተደረገ ወጪው ከዚህ በታች ሊሆን ይችላል ብለዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በበኩላቸው፤ ዝናብ አጠር በሆኑ ሁሉም አካባቢዎች ፕሮጀክቱን ተግባራዊ በማድረግ የራሱንና እንስሳቱን ሕይወት መታደግ ይቻላል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ ለጓሮ አትክልትና ለሌሎች አገልግሎቶችም የሚበቃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቦረና ዞን በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በድርቁ ምክንያት ከዚህ ቀደም ሲጠቀሙበት የነበረው የውሃ አማራጭ ሁሉ ደርቆ ሲቸገሩ እንደነበር አስታውሰው፤ ፕሮጀክቱ መፍትሔ ሆኖ መምጣቱን ተናግረዋል።

በቀጣይ የሚያዘውን ውሃ ለማጣራት ያሉ አማራጮች ላይ የማስተማርና የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚሰራ የተገለጸ ሲሆን፤ የዝናብ ውሃ የማሰባሰብ ሂደቱ የውሃ ማቆሪያ (ጂኦ-ሜምብሬን)፣ ቆርቆሮ፣ ምስማር፣ የጸሀይ ሀይል ማመንጫ (ሶላር)፣ ውሃ መሳቢያ (ትሪድል ፓምፕና) የመሳሰሉት ግብዓቶች ጥቅም ላይ ይውላሉ ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም