የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማረጋገጥ በህዝቦች ተሳትፎና ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም መገንባት ይገባል

138

ጋምቤላ ፤ መስከረም 24/2015 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያን አሸናፊነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በህዝቦች እኩል ተሳትፎና ፈቃድ ላይ የተመሰረተ የፌዴራሊዝም ስርዓት መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ።

"ኢትዮጵያ ታሸንፋለች" በሚል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሃመድ ባቀረቡት ጽሁፍ "የኢትዮጵያን አሸናፊነት ይበልጥ ለማረጋገጥ በህዝቦቿ ፈቃድና እኩል ተሳትፎ የተገነባ እውነተኛ የፌዴሊዝም ስርዓት መገንባት ሲቻል ነው" ብለዋል።

በህዝቦች ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ፌዴራሊዝም ስርዓት ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሀገር እድገትና ብልጽግና ዓይነተኛ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ባሉባት ሀገር ብዝሃነትን፣ የህዝቦችን ውክልና አምኖ ያለመቀበልና እኩል የልማት ተጠቃሚ ያለመሆን ችግር ለኢትዮጵያ ፈተና ሆኖ መቆየቱን አውስተዋል።

ኢህአዴግ በንድፈ ሃሳብ ‘‘የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር ነኝ’’ ይበል እንጂ በተግባር ሲታይ አግላይ እንደነበር አስረድተዋል።

ለዚህም ጋምቤላን ጨምሮ አራት ክልሎችን አጋር በማለት ፍትሃዊ ውክልና ተነፍጓቸው መቆየቱ ዋነኛ ማሳያ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ድርጅቱ እውነተኛ ያልሆነ ፌዴራሊዝም ሲከተል እንደነበረ አመልክተዋል።

የኢትጵያን አሸናፈነት ይበልጥ ለማረጋገጥ አሁን እየተገነባ ያለውንና ሁሉም ብሄረሰቦች ፍትሃዊ ውክልና ያለው እውነተኛ ፌዴራሊዝም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

አሸናፊ ህዝብና ሀገር ሆኖ ለመቀጠል ብቸኛው አማራጭ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በተሻለ መንገድ እየገነቡ መሄድ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የመወያያ ጹሁፍ አቅራቢ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው።

በኢትዮጵያ የህብረ ብሄራዊ አንድነት ተፈጥሯዊ እሴት ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ ኢትዮጵያ በአድዋ፣ በህዳሴ ግድብ ግንባታና በቅርቡ በውስጥና በውጭ ታሪካዊ ጠላቶች የተቃጣውን ሴራ በአሸናፊነት የመሻገሩዋ ምስጢር ህብረ ብሄራዊ አንድነት ነው ብለዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው፤ጥንትም ሆነ ዛሬ የኢትዮጵያ የአሽናፊነት ምስጢር ህዝቦቿ በአንድነት ጸንተው የመቆማቸው ታሪካዊ እሴት መሆኑን ገልጸዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሁሴን አህመድ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፊት 27 ዓመታት በወጣቱ ትውልድ የተዘሩ የአካባቢያዊ አስተሳሰቦች ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚጎዳ በመሆኑ እንዲስተካከሉ ብዙ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም