የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ በሰሞኑ ችግር የተፈናቀሉ ወገኖችን ጎበኙ

116
አዲስ አበባ መስከረም 11/2011 የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራችና ፕሬዝዳንት ኦባንግ ሜቶ ከቡራዩ ከታና ከሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለው በዊንጌት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የተጠለሉ ዜጎችን ጎበኙ። እንዲህ አይነቱ አስነዋሪ ተግባር የኢትዮጵያ መገለጫ ባለመሆኑ ልንታገለው ይገባል ብለዋል አቶ ኦባንግ። ጥቃት አድራሾቹ ተለይተው መታወቅና ድርጊቱ እንዳይደገም ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። ችግሩ በዘላቂነት መፍትሄ የሚያገኘው ሁሉም ዜጋ ሰውን በሰውነቱ ብቻ ተቀብሎ ከዘረኝነት ሲርቅ ብቻ ነው ብለዋል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመላው አገሪቱ የትኛውም አካባቢ የመኖር መብቱ ሊጠበቅ ይገባል ያሉት አቶ ኦባንግ ዘረኝነትን መጠየፍና አንድነትን መስበክ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ነው ያሉት። ድርጅታቸውም እንደ ሰብአዊ መብት ተቋም የራሱን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም