የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከስደት ተመላሽ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ከሁለት ሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር ተፈራረመ

390

መስከረም 23/2015 /ኢዜአ/  የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከስደት ተመላሽ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ከሁለት ሀገር በቀል ድርጅቶች ጋር ተፈራረመ፡፡

ሚኒስቴሩ ስምምነቱን የተፈራረመው “ፈርስት ኮንሰልት ኢትዮጵያ” እና “ጃምቦ የጽዳት አገልግሎት” ከተሰኙ ድርጅቶች ጋር ነው፡፡

የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ስምምነቱ በቅድመ ትግበራ ደረጃ 5 ሺህ የሚሆኑ ከስደት ተመላሽ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

በቀጣይም ከስደት ተመላሽ የሆኑ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በስምምነቱ መሰረትም በውጭ ሀገራት ክህሎት ቀስመው ወደ አገር ቤት ለመጡ ከስደት ተመላሽ ዜጎች ተጨማሪ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲሰማሩ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

በስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ከስደት ተመላሽ ዜጎችን ወደ ስራ ለማሰማራት እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ሰምምነቱም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ስራው በአገር አቀፍ ደረጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በተለይ ህገ-ወጥ ስደት በስፋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎችን በመለየት የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ጃምቦ ጽዳት አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ገብርዬ፤ በስምምነቱ መሰረት ከስደት ተመላሽ ዜጎች በጽዳት ዘርፍ የስራ እድል እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

በቀጣይም የስራ እድል ተጠቃሚ ዜጎችን ቁጥር ከፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

ለስደት ተመላሾች ስልጠና በመስጠት የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚሰራ የተናገረው ደግሞ የፈርስት ኮንሰልት ኢትዮጵያ የቡድን መሪ አቶ ሄኖክ ጠና ናቸው፡፡

በስምምነቱ መሰረት በተለይ ሴቶች የስራ እድል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ ተቋማቸው ለስራ ዝግጁ የሚያደርግ ስልጠና እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ መያዙን ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡