አገራዊ ለውጡ ለሶማሌ ክልል የመልማት እድልን የሰጠ ነው- የአገር ሽማግሌዎች

87

መስከረም 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተተገበረው አገራዊ ለውጥ ለሶማሌ ክልል የመልማት እድል የሰጠ መሆኑን የክልሉ የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ፡፡

የሶማሌ ክልል ሰፊ የመልማት አቅምና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ያለው ቢሆንም ቀደም ሲል በነበረው የመንግሥት አስተዳደር ተጎጂ ሆኖ መቆየቱንም አስታውሰዋል።

እየተተገበረ ያለው አገራዊ ለውጥን ተከትሎ በክልሉ በሁሉም መስክ ተጨባጭና የሚታዩ ውጤቶች መመዝገባቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ የአገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል።

የክልሉ ሕዝብ ከኢኮኖሚ ልማት በተጨማሪ በማህበራዊ እና ፖለቲካ ተሳትፎ ጭምር የታቀፈበት ታሪካዊ አጋጣሚ መፈጠሩን ገልጸዋል።

በዚህም በክልሉ ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩና የሕዝቡ የልማት ተሳትፎ በመጠናከሩ በተለይም በትምህርት፣ በመንገድ መሰረተ-ልማት፣ በግብርና እና ሌሎችም መስኮች የላቀ ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት የአገር ሽማግሌዎቹ።

ከክልሉ የአገር ሽማግሌዎች መካከል ሱልጣን አብዲ ፋራህ፤ የክልሉ ሕዝብ ተረጋግቶ ልማት ላይ ማተኮር እና የልማቱ ተጠቃሚ መሆን የጀመረው ባለፉት አራት ዓመታት መሆኑን ይናገራሉ።

በዚህም በሶማሌ ክልል በሁሉም መስክ የሚታዩ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የክልሉ የአገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት የሰላምና የአንድነት ኮሚቴ ምክትል ጸሐፊ ኡጋዝ አሊ ቦሮው፤ አገራዊ ለውጡ በተለይም ለሶማሌ ክልል የመልማት እድል የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የክልሉ ሕዝብ በተለያዩ መስኮች ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለስኬቱም በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅርና የሕዝቡ የላቀ ተሳትፎ መሆኑን ተናግረዋል።

ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት የመንግሥት ጥረት እንዳለ ሆኖ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችንና አጠቃላይ ሕዝቡ በትብብር በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም