ቅሬታ የሚነሳባቸውን የመሬት ነክ ጉዳዮችና የሕግ ክፍተቶችን በፍጥነት ለመፍታት እየተሰራ ነው-የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ

215

መስከረም 23 / 2015 (ኢዜአ) በኅብረተሰቡ ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚነሳባቸውን መሬትና የመሬት ነክ ጉዳዮችና የሕግ ክፍተቶችን በፍጥነት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው በከተማዋ ለሚገኙ 350 አቃቢያነ ህግ በመሬትና የመሬት ነክ ጉዳዮች፣ የመሬት ወረራ እንዲሁም የፍርድ ቤት እግድ ጋር በተያያዘ ለስድስት ቀናት የሚቆይ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

በስልጥና ማስጀመሪያው የተገኙት የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ጽዋዬ ሙሉነህ፤ በከተማ አስተዳደሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተብለው ከሚነሱት ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው መሬትና የመሬት ነክ አስተዳደር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በመዲናዋ በመሬትና የመሬት ነክ ጉዳዮች ላይ ለሚቀርቡ ቅሬታዎችና የህግ ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

በልማት ለሚነሱ ዜጎች በቂ ካሳ ካለመክፈል ጋር በተያያዘ ለሚቀርቡ ቅሬታዎችና ሌሎችም የህብረተሰቡን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የቢሮ ኃላፊዋ አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ አቃቢያነ ህግ በመሬት ዙሪያ ለሚነሱ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩ ይደረጋል ነው ያሉት ኃላፊዋ።

ከዚህ ባሻገር ህብረተሰቡን በሚያጉላሉ ባለሙያዎች ላይ ተገቢው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ጠቁመዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ደጀኔ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ አቃቢያነ ህግ የመንግስትን ሀብት ከማስመለስ በተጓዳኝ የህብረተሰቡን ቅሬታ በአግባቡ በመረዳት ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

 ህጋዊ አሰራረን ተከትለው እንዲሰሩና ከአድሏዊነት ነጻ በሆነ መንገድ ጉዳዮችን እንዲመለከቱም ተገቢው ሙያዊ እገዛ እየተደረገላቸው መሆኑን በማንሳት።

ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎችና የህግ ክፍተቶች  በጥናትና ምርምር በመታገዝ ለመፍታት ከፌደራል ፍትህና ህግ ኢኒስቲትዩት ጋር በመቀናጀት በችግሩ ላይ ያተኮሩ የዳሰሳ ጥናቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ በፍትህ ስርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆን የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ቀልጣፋ አሰራሮች በመዘርጋት እየተሰራ ነውም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም