ለፍኖተ ካርታ ትግበራና ውጤታማነት መምህራን በባለቤትነት ሊሠሩ እንደሚገባ ተመለከተ

63
ዲላ መስከረም 11/2011 ለአዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ትግበራና ውጤታማነት መምህራን በባለቤትነት ሊሠሩ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ ለፍኖተ ካርታው ገንቢ ምክረ-ሀሳቦችን ከምሁራኑ ለማግኘት ዓላማ ያደረገ የምክክር መድረክ በዲላ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ተወካይ ፕሬዘዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ በዚህ ወቅት እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት በሀገር ደረጃ በትምህርት ተደራሽነት ላይ በትኩረት ሲሰራ ቢቆይም በዚህ ልክ ጥራቱን ማስጠበቅ አልተቻለም፡፡ የትምህርት ጥራቱ  አሁን ባለበት ደረጃ ደግሞ ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ የሚደረገው ጉዞ መሰናክል እንደሆነ  አመልክተዋል፡፡ አዲሱ ፍኖተ ካርታ ያጋጠሙትን  ችግሮች ለመፍታት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ጠቁመው የትምህርት ተቋማት በቂ ድጋፍ እንዲያገኙና የተሳለጠ አስተዳደር እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስረድተዋል፡፡ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ እቅዶችን ከወዲሁ ማዘጋጀቱና በምሁራን ምክረ-ሀሳቦች ዳብሮ እንደሚተገበር  ዶክተር ችሮታው ገልጸዋል፡፡ ለፍኖተ ካርታ ትግበራና ውጤታማነት መምህራን በባለቤትነት ሊሠሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የግንባታ ቴክኖሎጂ አስተዳደር ምህንደስና ትምህርት ክፍል መምህር ሙሉጌታ አቡዬ አዲሱ በበኩላቸው "የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ በተለይ ለምህንድስና ተማሪዎች ጠቀሜታው የጎላ ነው "ብለዋል፡፡ ምምህሩ እንዳሉት በተግባር ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ የምህንድስና ተማሪዎች ለተግባር ልምምድ የሚመደብላቸው ጊዜ አጭር በመሆኑ ከሥራው ጋር መተዋወቅ እንዳልቻሉ አስታውሰዋል፡፡ አዲሱ ፍኖተ ካርታ ይህን የተግባር ልምምድ ጊዜ ለማራዘም ያለመ መሆኑ ተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ ያካበቱትን እውቀት በተግባር የሚያዳብሩበትን ሰፊ እድል ይፈጥራል፡፡ የዚሁ ትምህር ክፍል መምህር አድማሱ አበበ አሁን ላይ በየአካባቢው ለሚስተዋሉ የግንባታ ፕሮጀክቶች መጓተትና የጥራት መጓደል ችግሮች ዋንኛ ምክንያት ተቋማት በዘርፉ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት አለመቻላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ ፍኖተ ካርታ ለነዚህ ችግሮች መፍትሔ ሊያበጁ የሚችሉ ሀሳቦችን ማካተቱን የተናገሩት መምህሩ "ውጤታማ እንዲሆን ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል "ብለዋል ፡፡ ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ዘርፍ አስተባባሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም