በዞኑ በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው መሬት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዬን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርጥ ዘር ለማግኘት ታቅዷል

128

ጭሮ ፤መስከረም 23/2015 (ኢዜአ) በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው 30 ሺህ ሔክታር መሬት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዬን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርጥ ዘር ለማግኘት መታቀዱ ተገለጸ።

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን መሀመድ እንደተናገሩት በ2014 ዓ.ም መኸር እርሻ በዞኑ የ30 ሺህ ሔክታር በስንዴ ምርጥ ዘር ምርት ተሸፍኗል።

የአካባቢው አርሶ አደር ቀድም ባለው ጊዜ በሔክታር ከ10 እስከ 15 ኩንታል ብቻ እያመረቱ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዞኑ የስንዴ ምርጥ ዘር ማምረት ከተጀመረበት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን በሔክታር ከ45 እስከ 50 ኩንታል ምርት እየተገኘ ነው ብለዋል፡፡

የዞኑ ቆላማ ክፍሎችም ቢሆኑ ወደ ዘመናዊ የስንዴ ምርጥ ዘር ምርት እየገቡ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።

አብዛኛው የዞኑ አርሶ አደርም የኩታ ገጠም ግብርናን በመተግበርና ምርጥ ዘርን በመጠቀም ወደ ዘመናዊ ግብርና እየገባ መሆኑን አክለዋል።

በዞኑ ሚኤሶ ወረዳ ኦዳ በላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አብደላ እንድሪስ ከዚህ በፊት ለቀለብ ፍጆቷ  እንኳን የማይበቃ ምርት ሲያመርቱ መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡

አሁን የኩታ ገጠም አስተራረስ ስርዓትን በመከተላቸው ምርትና ምርታማነት ማደጉን መስክረዋል።

''ስንዴ በአጭር ጊዜ የሚደርስ በመሆኑ አካባቢያችን የሚከሰተው የዝናብ እጥረት ችግር እንዳይሆንብን አግዞናል'' ብለዋል።

አርሶ አደር ኡስማን ኡመር በበኩላቸው በአካባቢያቸው በሚከሰት የዝናብ ማጠር ሳቢያ የምርት መጠን ማነስና አንዳንዴም ከነጭራሹ ፍሬ ሳይዝ መቅረት ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡

የስንዴ ምርጥ ዘርን ማምረት ከጀመሩ ወዲህ ከቀለብ አልፈው ከፍተኛ የምርት መጠን ማግኘት መጀመራውን ገልጸዋል፡፡

ሌሎች የአካባቢ አርሶ አደሮችም ምርት እየጨመረ በመምጣቱ በምግብ ራሳቸውን እየቻሉ ምርታቸውንም ለገበያ እያቀረቡ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም