የ12ኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተሳካ መልኩ ለማከናወን በቂ ዝግጅት ተደርጓል- ትምህርት ሚኒስቴር

227

መስከረም 23/2015 (ኢዜአ)  የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተሳካ መልኩ ለማከናወን በቂ ዝግጅት መደረጉን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ተፈታኝ ተማሪዎችን ወደሚፈተኑበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የማጓጓዝ ስራውን የክልል የጸጥታ ተቋማት ኃላፊነት ወስደው እየሰሩ መሆኑም ተናግረዋል።

ወደ መፈተኛ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተፈታኞች ከገቡ በኋላም ማንኛውንም አይነት ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ስራ በፌደራል ፖሊስ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ዘጠኝ መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማጓጓዝ በሁለት ዙር ለፈተና እንደሚቀመጡም ጠቁመዋል።

የፈተና ዝግጅቱም በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘና ዘመናዊ ስርዓትን የተከተለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፈተናውም  በዩኒቨርሲቲ መምህራን እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

ይህም ኩረጃን በማስቀረት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንደሚረዳ ነው ያነሱት፡፡

ፈተናውን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለማጠናቀቅም የፌደራልና የክልል የጸጥታ አካላት ክትትል፣ ድጋፍና ቁጥጥር እንደሚያደርጉም እንዲሁ፡፡

በዚህም የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ከመስከረም 26-28 ወደሚፈተኑባቸው ዩኒቨርሲቲዎች የሚገቡ ሲሆን ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 02 ፈተና ወስደው ከጥቅምት 03 ጀምሮ ወደመጡበት እንደሚመለሱ ተጠቅሷል።

ከጥቅምት 05 እስከ ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስም የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ዘርፍ ተፈታኞች ዩኒቨርሲቲ ገብተው ፈተናውን የሚያጠናቅቁበት የጊዜ መርሀ-ግብር መውጣቱንም ተገልጿል።

ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ የጸጥታ አካላት እና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ፈተናው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ ቀርቧል።

፤የመጀመሪያ ዙር የ2014 ዓ.ም የመልቀቂያ ፈተናን መውሰድ ያልቻሉ ከ56 ሺህ በላይ ተማሪዎች የመጀመሪያው ዙር ፈተና በተጠናቀቀ በአንድ ወር ጊዜ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም