በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የአግር ኳስ ውድድር ዛሬ ይጀመራል

188

መስከረም 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ዛሬ ይጀመራል።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ብሩንዲ፣ ታንዛንያ፣ ዩጋንዳና ሶማሊያ ይሳተፋሉ።

በመክፈቻው ቀን ከቀኑ 7 ሰዓት በምድብ አንድ ዩጋንዳ ከብሩንዲና በምድብ ሁለት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ከቀኑ 10 ሰአት በአበበ በቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር 10 አገራት ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ተገልጾ ነበር።

ኤርትራ፣ ርዋንዳ፣ ሱዳንና ጅቡቲ በተለያየ ምክንያት ከውድድሩ ውጪ በመሆናቸው ምክንያት የተሳታፊ አገራት ቁጥር ወደ ስድስት ዝቅ ብሏል።

የተሳታፊ አገራት ቁጥር በመቀነሱ የምድብ ድልድል ዕጣ ትናንት በድጋሚ መውጣቱ ይታወቃል።

የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።

በውድድሩ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ አገራት ሴካፋ ዞንን ወክለው በመጪው መጋቢት ወር በአልጄሪያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ዋንጫ ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም