በጋምቤላ ክልል በመኸር ወቅት ባጋጠመው ጎርፍ የታጣውን የግብርና ምርት በበጋው ልማት ለማካካስ እየተሰራ ነው

119

ጋምቤላ ፤ መስከረም 21/2015(ኢዜአ) ፡- በክልሉ በመኸር ወቅት ባጋጠመው ጎርፍ አደጋ የታጣውን ምርት በበጋው የግብርና ልማት ለማካካስ ከወዲሁ በመዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በክረምቱ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከ43 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ ሰብል ላይ ጉዳት  መድረሱ ተመልክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አጃክ ኡጃላ ለኢዜአ እንዳሉት፤እንደ ሀገር የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም በ2014/ 2015 የምርት ዘመን ሰፊ የግብርና ልማት ንቅናቄ በመፍጠር ወደ ስራ ተገብቶ  ነበር።

ሆኖም ክልሉ ተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከፍተኛ ተፀዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በምርት ዘመኑ ከ148 ሺህ 780 ሄከታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ131 ሺህ365 ሄከታር በላይ መከናወኑን አውስተዋል።

ይሁን እንጂ ባሮ ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ትላልቅ ወንዞች ሞልተው በመፍሰስ ባስከተሉት የጎርፍ አደጋ ከ43 ሺህ ሄከታር በላይ ሰብል መውደሙን ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት የታጣውን ምርት በበጋው የግብርና ልማት ለማካካስ  ከወዲሁ በመዘጋጀት እየተሰራ  መሆኑን ነው ኃላፊው ያስታወቁት።

በተለይም በበጋው የግብርና ልማት ውሃ ሸሽ/እርጥበታማ አፈርን/ አነስተኛ መስኖዎችንና ሌሎች የውሃ አመራጮችን በመጠቀም ከ40 ሺህ ሄክታር መሬት  ለማልማት መታቀዱን አቶ አጃክ ተናግረዋል።

ለበጋው የግብርና ልማት ስራው የምርጥ ዘር፣ የውሃ መሳቢያ ፓምፖችና ሌሎች የግብርና ግብዓቶችን ለማቅረብም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በጋምቤላ ከተማ ዙሪያ በግብርና ልማት ከተሰማሩት አርሶ አደሮች መካከል አቶ አቡላ ኡጀር በሰጡት አስተያየት፤  የባሮ ወንዝ ሞልቶ በመፍሰስ ባስከተለው ጎርፍ በደረሰ ስብላቸው ላይ ጉዳት ማድረሱን  ተናግረዋል።

በምርት ዘመኑ  ካለሙት የበቆሉ ሰብል ከ45 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ቢያቅዱም በጎርፍ ስለተበላባቸው ምርቱ በግማሽ መቀነሱን ገልጸዋል።

በጎርፉ ያጡትን ምርት በበጋው የግብርና ልማት ለማካካስ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

የባሮ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ የእርሱን ጨምሮ በቀበሌያቸው እስከ 60 የሚደረሱ   አርሶ አደሮች ሰብል መውደሙን የገለጹት ደግሞ ሌላው የጋምቤላ ከተማ ዙሪያ አርሶ አደር ወጣት ኡጆድ ዲድሙ ነው። 

ውሃ ከሸሸ በኋላ እርጥበታማ አፈርን በመጠቀም በቆሎ፣ ማሽላና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በማልማት በመኸር እርሻ ያጣውን ምርት ለማካካስ  እንደሚሰራ ነው ወጣቱ የተናገረው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም