በትግራይ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል እየተሰራ ነው

97
መቀሌ መስከረም 11/2011 በትግራይ ክልል የክረምት መውጣትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ 35 ወረዳዎች ለወባ በሽታ ወረርሽኝ ተጋላጭ መሆናቸውም ተመልክቷል። በክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የወባ በሽታ መከላከያ አማካሪ አቶ ገብረመድህን ክንፈ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የክረምቱ መውጣትን ተከትሎ  ሊከሰት የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከል ከወዲሁ እየተሰራ ነው። በክልሉ ከሚገኙ 52 ወረዳዎች ውስጥ 35ቱ ለወባ ወረርሽኝ ተጋላጭ መሆናቸውንም ጠቁመዋል። በወረዳዎቹ ከሚገኙ ነዋሪዎች አብዛኞቹ ለበሽታው የሚጋለጡ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ገብረመድሀን፣ ወረዳዎቹን ከወባ በሽታ ወረርሽኝ ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ወባ በወረርሽኝ መልክ ቢከሰት ይበልጥ ሊጎዱ በሚችሉ 12 ወረዳዎች በሚገኙ 180 ሺህ መኖሪያ ቤቶች የወባ መከላከያ ኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህም በወረዳዎቹ የሚኖር ከ360 ሺህ በላይ ህዝብ ከወባ ማስተላለፊያ ትንኝ ነጻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ለመከላከል ሥራውም ከ180 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የወባ በሽታ መከላከያ ኬሚካል ጥቅም ላይ መዋሉንና ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ መንግስት ወጪ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ በ15 ወረዳዎች 346 ሺህ 870 የወባ ትንኝ መከለከያ አጎበር በማሰራጨት ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ከወባ በሽታ ለመጠበቅ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡ የወባ በሽታ በክልሉ ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች በመጀመሪያ ተርታ ይጠቀስ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ገብረመድህን፣ ባለፉት ሦስት ወራት በወባ በሽታ 28 ሺህ ሰዎች ተይዘው ሁሉም ታክመው መዳናቸውን ገልጸዋል፡፡ በየዓመቱ በተካሄደው የኬሚካል ርጭት፣ የአጎበር እደላና ህብረተሰቡ ተቀናጅቶ በሚያደርገው እንቅስቃሴ በወባ የሚያዙ ነዋሪዎች ቁጥር በ28 በመቶ አንዲቀንስ ለማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡ ህብረተሰቡ በውጭ ምንዛሬ ተገዝቶ የሚመጣውን አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀምበት አማካሪው አስገንዝበዋል፡፡ መንግስት በሚያቀርብላቸው አጎበር ከወባ በሽታ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በመጠበቅ ሙሉ ጊዜያቸውን ሥራ ላይ ለማሳለፍ እንዳስቻላቸው የተናገሩት ደግሞ በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ የሐይቅ መሳህል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ገብረክርስቶስ ፍሰሃ ናቸው፡፡ በመንግስት ከሚያቀርብላቸው መከላከያ አጎበር በተጨማሪ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማዳፈንና የትንኝ መራቢያ ረግረጋማ ቦታዎችን የማፋሰስ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የወባ በሽታን ለመከላከል በልማት ቡድን ተደራጅተው አካባቢያቸውን የማጽዳት ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን  የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ዓመተብርሃን ታረቀ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው። እየተገባደደ ያለውን የክረምት ወቅት ተከትሎ በርካታ ቦታዎች ውሃ ማቆራቸውን ገልጸው፣ ከሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ቦታዎቹን የማዳፈን ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም