የኢሬቻ በዓል አከባበር በርካታ አስደናቂ፣ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች የያዘ ነው- ሀዳ ሲንቄ አፀዱ ቶላ

234

መስከረም 20/2015/ኢዜአ/የኢሬቻ በዓል አከባበር በርካታ አስደናቂ፣ ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች የያዘ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ሀዳ ሲንቄ አፀዱ ቶላ ገለጹ።

የኢሬቻ በዓል አከባበር በርካታ መገለጫዎች ያሉት ሲሆን በዓሉ በሚከበርበት ቦታ ሲኬድ ሴቶች ከፊት የሚጓዙበት ሥርዓት ከእሴቶቹ መገለጫዎች መካከል ይጠቀሳል።

ወደ ወንዝ ወይም ሐይቅ ሲኬድ እርጥብ ሣር በመያዝ “መሬዎ መሬዎ” እያሉ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ይሄዳሉ።

በዚህም ምስጋና፣ ሰላም፣ እርቅን፣ መልካም ምኞትን፣ ስኬትን፣ ብልፅግናን እና አንድነት የሚሰበክበት በዓል ነው።

የተጣሉ ሰዎች በዓሉ በሚከበርበት ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ቀደም ብለው እርቅ በማውረድ የሚታደሙበት ነው።

ሁሉን አድራጊ የሆነውን የፈጣሪያቸውን ኃይል የሚገልጹበትና የሚያወድሱበት የመልካ ኢሬቻ በዓል የመስቀል በዓል ካለፈ በኋላ በመፀው ወቅት ይከበራል።

የክረምት ወራት ጭቃና ረግረግ፣ ዝናብ አልፎ ወንዝ ጎድሎ ሰዎች የሚገናኙበት ወቅት በመሆኑ ለዚህም ሰዎች ምስጋና ያቀርባሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ሀዳ ሲንቄ አፀዱ ቶላ፤ የኢሬቻ በዓል አከባበር ላይ ሰላምን የሚያወርዱና እርቅ እንዲመጣ የሚለምኑ ሀዳ ሲንቄዎች ከአባ ገዳዎች ፊት በመሄድ ወደ መልካ የሚደረገውን ጉዞ የሚመሩ መሆኑን ይናገራሉ።

በመሆኑም በገዳ ሥርዓት የሴቶች እኩልነትና ክብር በተግባር የሚገለጽበት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

“የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ቦታ ላይ በንጹህ ልብ ምስጋና ይቀርባል፤ ምህረትም ይለመናል።” ያሉት ሀዳ ሲንቄ አፀዱ፤ በዚህም የፈጣሪ ስጦታ የሆነውን እርጥብ ሣር በመያዝ ወደ ወንዝ የሚኬድ መሆኑን ያስረዳሉ።

በበዓሉ አከባበር ውሃማ አካላት ምስጋና ለማቅረብ የተመረጠበት ምክንያት “ውሃ ለሁሉም ነገር ጠቃሚ ህይወት” በመሆኑ ነው ይላሉ።

በመሆኑም በፀደይ ወቅት ወደ ውሃማ አካላት በመሄድ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢሬቻ በዓል የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የአብሮነት መሆኑን ደግሞ አቶ ቁፋ ጉቤ ይናገራሉ።

ኢሬቻ ኢትዮጵያ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው  መካከል የሆነው የገዳ ሥርዓት አካል መሆኑ ይታወቃል።