እኛ ኢትዮጵያውያን ለየትኛውም ምድራዊ ኃይል አንንበረከክም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

159

መስከረም 20 ቀን 205(ኢዜአ) “እኛ ኢትዮጵያውያንን የትኛውም ምድራዊ ኃይል አያንበረክከንም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

“ብዙ ነጻነታችንንና ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተኑ ነገሮች ቢኖሩም ከመንገዳችን ሊያሰናክሉን አይችሉም”ም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢሬቻ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

“ኢሬቻ የወንድማማችነት/እህትማማችነት የአንድነት ቀን፣ ወንድማማችነት/እኅትማማችነት የሚጠነክርበትና የፍቅር የወዳጅነት በጋራ የመኖር ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል በዓል ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

በታሪክ ውስጥ በአንድነት እንጂ በልዩነት ተከብረን ተፈርተንም ሆነ አሸንፈን አናውቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ሆነን ስንቆም በሁሉም ግንባር ድልን እንደምንጎናጸፍና የትኛውንም የሚሸረብብንን ሴራ ማክሸፍ እንደምንችል በግልጽ ማሳየት ችለናል ብለዋል።

ያለፈው አራት ዓመት የተደቀኑብንን ፈተናዎች በጋራ ማለፍ እንደሚቻል ማሳየቱን አመልክተዋል።

“ጠላቶቻችን ወድቀዋል ሲሉን ተነስተን ፈርሰዋል ሲሉን ተገንብተን አይተውናል፤ አሁንም ብዙ ነጻነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተኑ አሉ፤ ከመንገዳችን ግን ሊያሰናክሉን አይችሉም” ነው ያሉት።

“ሐቅ አለን እውነት ላይ ቆመን እንታገላለን ፈጣሪም ከኛ ጋር ነው፤እኛ ኢትዮጵያውያን ለየትኛውም ምድራዊ ኃይል አንንበረከክም” ብለዋል።

ትልቁ ጠላታችን የሆነውን ድህነት ለማሸነፍ መሥራት እንደሚገባና የሥራ ባህላችንን በማሻሻል በሁሉም የልማት መስኮች በመሰማራት ለማሸነፍ በቁጭት መትጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን እንደ ኢሬቻ ያሉ ታላላቅ ክብረ በዓላትን እንደ አንድነታችን ማጠናከሪያ መሳሪያ ይዘን በአጭርና በረዥም ጊዜ የያዝነውን የብልፅግና ጉዟችንን ለማደናቀፍ የተከፈተብንን ዘመቻዎች ሁሉ ጥሰን በማለፍ የያዝነውን ራእይ ለማሳካት በአንድነት እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው “የዘንድሮ ኢሬቻ ወደ አዲስ ምዕራፍ የምንሸጋገርበትና በድል ላይ ድል የምናስመዘግብበት እንዲሆንልን እመኛለሁ” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም