አሸባሪው ሕወሓት የተመድና የዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶችን ንብረቶች ለጦርነቱ እየተጠቀመ ነው - የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ

127

መስከረም 20 / 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሓት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና የዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶችን ንብረቶች ለጦር መሳሪያ ማጓጓዣና ማከማቻነት በመጠቀም ለጦርነት እያዋለ መሆኑን የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ አስታወቀ።

የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ በማህበራዊ ትስስር ገጹ እንዳስታወቀው የሽብር ቡድኑ የእምነት ቦታዎችን፣ መኖሪያ አካባቢዎችንና ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የጦር መሳሪያ ማከማቻ አድርጓል።

May be an image of outdoors

የኢትዮጵያ መንግስት አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ዳግም የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ የመከላከል እርምጃዎችን በመወሰድ ላይ እንደሚገኝ የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገልጿል።የኢፌዴሪ አየር ኃይል ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ተጨማሪ ጉዳት ሳይደርስ የሽብር ቡድኑን የወታደራዊ አቅሞች ብቻ በተሳካ ሁኔታ እየመታ እንደሚገኝ አመልክቷል።

አየር ኃይሉ በቅርቡ በትግራይ ክልል አዲ ዳእሮ የሽብር ቡድኑ የጦር መሳሪያዎችና ማከማቻዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ጠቁሟል።

አሸባሪው ሕወሓት አመራሮቹንና የጦር መሳሪያዎቹን በእምነት ቦታዎች፣ በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች፣ በመኖሪያ ቤቶችና በሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎች በመደበቅ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን በማሸበር ላይ ይገኛል ነው ያለው የማጣሪያ ገጹ ባወጣው መረጃ።

የሽብር ቡድኑ ዜጎች የሚኖሩባቸውና የሚሰበሰቡባቸውን ቦታዎች ለጦርነት ከለላ እየተጠቀመ የሚገኘው “በንጹሃን ዜጎች ላይ ይደርሳል ብሎ ያሰበው ጥቃት የዜጎችን ቁጣ ይቀሰቅሳል” በሚል አደገኛ አስተሳሰብ መሆኑን ገልጿል።

በተጨማሪም ቡድኑ የተመድ እና ሌሎች የዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ንብረቶችን ለጦር መሳሪያ ማጓጓዣነትና ማከማቻነት በማዋል ለጦርነት እየተጠቀመ እንደሚገኝ አመልክቷል።

“በአየር ጥቃቱ ንጹሃን ዜጎች ኢላማ ሆነዋል” በሚል የአሸባሪው ሕወሓት ደጋፊዎች የለመዱትን ሐሰተኛ ድርሰት እያስተጋቡ እንደሚገኙ ጠቅሷል።

እርምጃዎች ወታደራዊ ቦታዎችን ከዜጎች መለየታቸው ከተረጋገጠ በኋላ እንደሚወሰዱ ነው የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ ገጽ ያስታወቀው።

“አሸባሪው ሕወሓት ጦርነቱን ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች አውሮፕላንና መሳሪያዎች ለማስገባት ሙከራ አድርጓል።

በቅርቡ ቡድኑ ወደ ያዛቸው አካባቢዎች የጦር መሳሪያዎችን ሊያደርስ የነበረ አውሮፕላን ተመትቶ መውደቁ የሽብር ቡድን እኩይ ተግባር ዋንኛ ማሳያ ነው” ብሏል የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያው።

ከከሸፈው የመሳሪያ ማጓጓዝ ሙከራ በኋላ የኢትዮጵያ አየር ክልል በጥብቅ ክትልልና ቁጥጥር ውስጥ እንደሚገኝ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም