የኢሬቻ በዓል ሰላምን፣ አብሮነትን፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትንና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ሊከበር ይገባል- አባ ገዳዎች

146

መስከረም 20/2015 (ኢዜአ) የኢሬቻ በዓል ሰላምን፣ አብሮነትን፣ ኢትዮጵያዊ አንድነትንና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ሊከበር እንደሚገባ አባገዳዎች ጥሪ አቀረቡ።

የቱለማ አባገዳና የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ፀሐፊ ጎበና ሆላ እንዲሁም የጉጂ አባገዳና የኦሮሞ አባ-ገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ ጂሎ ማኖ ጋምቤሎ ለ2015 የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን ከመከራ ወደ ተስፋ-ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን አስመልክቶ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ስርዓት መሆኑን አባገዳ ጎበና ሆላ አብራርተዋል።

ኢሬቻ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የአንድነትና የመልካም ተግባር መገለጫ መሆኑን የሚናገሩት የጉጂ አባገዳና የኦሮሞ አባገዳዎች ሰብሳቢ ጂሎ ማኖ ጋምቤሎ በበኩላቸው እሴቱን በጠበቀ መልኩ ማክበር አለበት ብለዋል።

ኢሬቻ የገዳ ስርአት ነጸብራቅ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያውያንና የመላው ዓለም ቅርስ መሆኑን የጠቀሱት አባ ገዳ ጎበና፤ በበዓሉ ላይ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ዜጎች እንደሚታደሙ ጠቁመው ህዝቡም በዓሉን በሰላምና በአብሮነት እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል።

ህዝቡ ወደ በዓሉ ማክበሪያ ስፍራ ሲሄድ እርጥብ ሳርና ከለቻ ይዞ፣ የሀገር ባህል ልብስ ተለብሶ፣ የሰላም፣ የአብሮነትና የምስጋና ዝማሬ እየተዘመረ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

በበዓሉ ላይ ምንም አይነት ፖለቲካዊ መልዕክትና አርማዎችን ይዞ መገኘት ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑን ጠቅሰው፤ የህዝብን አንድነት የሚጻረር መልዕክት የሚያስትላልፍ ካለ በገዳ ስርዓት መሰረት የተወገዘ መሆኑን አስረድተዋል።

በዓሉ ኢትዮጵያዊ እሴት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንንም ማጉላት እንደሚገባ አባ-ገዳ ጂሎማኖ ጠቁመዋል።

ለበዓሉ ታዳሚዎችና እንግዶች ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት የምስጋናና የአብሮነት መገለጫ መሆኑን በተግባር ማሳየት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም