በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የተተከለ የመተንፈሻ አካል መመርመሪያ ማሽን ተመርቆ ስራ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የተተከለ የመተንፈሻ አካል መመርመሪያ ማሽን ተመርቆ ስራ ጀመረ
አርባ ምንጭ መስከረም 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የተተከለ የመተንፈሻ አካል መመርመሪያ ማሽን ተመርቆ ስራ ጀመረ።
የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እና የደቡብ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ዛሬ ማምሻውን ማሽኑን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ እንዳሉት ማሽኑ አሜሪካ ከሚገኘው ኦሀዮ /OHIO/ ዩኒቨርሲቲ በድጋፍ የተገኘ ነው።
ማሽኑ ኢንፍሉወንዛን ጨምሮ በርካታ የመተንፈሻ አካላት በሽታዎችን የመመርመር አቅም ያለው መሆኑን ጠቁመው ከዚህ ቀደም ማሽኑ በሀገር ውሰጥ ባለመኖሩ ናሙናዎች ወደ ውጭ ሀገር ሲላኩ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማሽኑን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በተደረገ ጥረት ማሽኑ በአዲስ አበባ፣ አዳማና ባህርዳር ከተሞች መተከሉንና ዛሬ በአርባምንጭ የተተከለው ማሽንም በሀገሪቱ አራተኛው መሆኑን ተናግረዋል።
በሆስፓታሉ ማእከል ውስጥ የተተከለው ማሽን ደቡብ ክልልን ማዕከል አድርጎ እንደሚያገለግልና በተለይ ለጋሞ፣ ለወላይታ፣ለጎፋ፣ለኮንሶና ለደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም ለአማሮ፣ቡርጂ፣አሌ፣ ደራሼና ባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን አስታውቀዋል ።
በምረቃ ሥነ ስርአቱ ላይ ኦሃዩ ስቴት ግሎባል ዋን ሄልዝ የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እና የጋሞ ዞን የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።