የአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

248

መስከረም 19 / 2015 (ኢዜአ) የአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።

በቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ሚኒስትሮች ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ አርቲስቶች፣ የድምጻዊው ወዳጆችና አድናቂዎች ተገኝተዋል።

በቀብር ስነ ስርዓቱ የጸሎት መርሃ ግብር ፣ የአርቲስቱ የስራ እና የሕይወት ታሪክ በአርቲስት አለሙ ተፈሪ ቀርቧል።

ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ስለ ሀገር፣ ታሪክ፣ ባህል፣ፍቅርና ሌሎች ጉዳዮች የሚዳስሱ መልዕክቶችን በማዜም በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ስራ ላይ የራሱን አሻራ አሳርፏል።

ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ወቅት እያመመው ግንባር ድረስ በመሄድና በማሰልጠኛ ተቋማትም በማነቃቃት የራሱ የሆነ ታሪክ የሰራ አርቲስት መሆኑም ይታወቃል።

በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሀገር አዘዞ ተወልዶ በደብረታቦር ያደገው አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ መስከረም 17/2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም