አሸባሪው ሕወሃት እየተከተለ ያለው የጥፋት መንገድ የትግራይ ህዝብን ለከፋ ችግር እየዳረገው ነው--በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች

122

መስከረም 19 ቀን 2015 (ኢዜአ)  አሸባሪው ሕወሃት እየተከተለ ያለው የጥፋት መንገድ የትግራይ ህዝብን ለከፋ ችግር እየዳረገው መሆኑን በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተናገሩ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የትግራይ ብልጽግና ፓርቲና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)አባላት፤ አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከፍተኛ በደል ሲፈጽም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያዊያን ትግል ከስልጣን ከተወገደ በኋላም "ኢትዮጵያን እኔ ካልመራኋት ትፍረስ" በሚል እሳቤ በአገር ህልውና ላይ አደጋ መደቀኑን ነው የተናገሩት፡፡

የሽብር ቡድኑ በትግራይ ህዝብ ላይ ከፍተኛ የአፈና መዋቅር በመዘርጋት ሰብዓዊ ጥሰት ሲፈጽም ቆይቷል፤ አሁንም በዚህ ተግባሩ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡

የትዴፓ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያ በስልጣን በቆየባቸው ጊዜያት የኢትዮጵያ ህዝብ በመራር ጭቆና እና አፈና ስርዓት እንዲያልፍ አድርጓል፡፡

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲፈጽም የነበረውን የጭቆና ፣አፈና  እና ዝርፊያ ስርዓት ለማስቀጠል ከፍተኛ ሴራ ሲያከናውን መቆየቱን አንስተዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በውይይትና ሃሳብ የበላይነት እንደማያምን የሚናገሩት አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ፤  የሽብር ቡድኑ ግጭት ቀስቃሽ ባህርይ የትግራይ ህዝብን ለከፋ ችግር እየዳረገው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሸባሪው ህዋሃት ከዴሞክራሲ የተጣላ ድርጅት ነው የሚሉት ኃላፊው፤ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ጊዜያት ከእርሱ የተለየ ሃሳብ በሚያራምዱት ላይ ከፍተኛ ግፍ ሲፈጽም መቆየቱን ለአብነት አንስተዋል፡፡

በተለይ የትግራይ ህዝብን የተለየ የሃሳብ አማራጭ እንዳያገኝ እድርጎ በአፈና ስርዓት ውስጥ መያዙን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ አሸባሪው ህወሃት ለትግራይ ህዝብ የችግር እንጂ የመፍትሔ አካል ሆኖ እንደማያውቅ አብራርተዋል፡፡

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ መስራችና አባል አቶ ባረያገብር አባይ በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ አሸባሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ የተሰጠውን የሰላምና የውይይት እድል አለመጠቀሙን ይገልጻሉ፡፡

መንግስት ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ረዥም ርቀት መጓዙን በመጥቀስ፡፡

የሽብር ቡድኑ የትግራይ ብልጽግና አባላትን ጨምሮ በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት አባላትን በመግደል ክልሉን ወደ ኋላ ሲመልሰው መቆየቱንም አክለዋል፡፡

በዚህም የትግራይ ክልል ነዋሪዎች መብታቸውን እንዳይጠይቁ ከፍተኛ ጫና ሲፈጥር ቆይቷል፤ አሁንም ይህን አፈና አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት፡፡

አሸባሪው ህወሃት በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመቀናጀት በአገር ህልውና ላይ አደጋ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ የሽብር ቡድኑን ሴራ ሊመክቱ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም