በአዳማ የድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎችን ለመታደግ የአንድ ማዕከል የአምቡላንስ አገልግሎት መስጠት ተጀመረ

99

አዳማ፤ መስከረም 19/2015(ኢዜአ) ፡-በአዳማ የድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎችን ለመታደግ የሚያግዝ የአንድ ማዕከል የአምቡላንስ ጥሪና ስምሪት አገልግሎት መስጠት ተጀመረ።

የሉቡ የአምቡላንስ ጥሪና ስምሪት ማዕከል የተሰኘው ይሄው አገልግሎት ዛሬ ተመርቆ ስራ በጀመረበት ወቅት    የአዳማ ኮፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልና ሜዲካል ኮሌጅ ዲን ዶክተር በቃና ለሜሳ እንደገለጹት፤  ሆስፒታሉ ባለፈው ዓመት ከ30 ሺህ በላይ  የድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎች ህክምና ሰጥቷል።

የመንግስት የሆነው ሆስፒታሉ አርሲ ዞን ምስራቅና ማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞኖችን እንዲሁም አማራና አፋር ክልሎች ለሚመጡ መደበኛና ድንገተኛ ተካሚዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተለይ አብዛኛው የድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎች ፈጣን ህክምናና የአምቡላንስ አገልግሎት በወቅቱ ማግኘት ባለመቻላቸው  አደጋ በደረሰበት ቦታ ህይወታቸው ያልፋል ነው ያሉት ።

በ8 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደራጀ የአምቡላንስ ጥሪና ስምሪት ማዕከል ከ16 እስከ 20 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ውስጥ ለድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎችና ታማሚዎች 24 ሰዓት አገልግሎት በመስጠት ህይወትን ለመታደግ እንደሚያግዝ አስረድተዋል ።

ለዚህም ነፃ የአምቡላንሶች አገልግሎትን  በ9655 ነፃ የስልክ ጥሪ መስጠት የሚያስችል ማዕከል መደራጀቱን ዶክተር በቃና ለሜሳ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም 100 ወጣቶች በድንገተኛ የመጀመሪያ ዕርዳታ ህክምናና አገልግሎት ላይ እየሰለጠኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ቦኮና ጉታ በበኩላቸው፤ ለክልሉ የመጀመሪያ የሆነው ማዕከሉ  ለድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎች ፈጣን ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የጤና አገልግሎትን ለማሻሻልና በድንገተኛ አደጋ የሚከሰት ሞት ለመቀነስ  የአምቡላንስ ተሽከርካሪዎች ለተፈቀደው አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ ለማስቻል ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል ።

አብዛኛው የድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎች ህይወት የሚያልፈው አደጋው በደረሰበት ቦታ መሆኑን ጠቅሰው፤  ችግሩን ለማቃለል የአንድ ማዕከል የአምቡላንስ ጥሪና ስምሪት ማዕከል መከፈቱ  ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዳማ ተጨማሪ ጠቅላላ ሆስፒታልና  የቀዶ ጥገና ክፍሎች ለመገንባት የዲዛይን ስራ መጠናቀቁንም ጠቁመዋል።

ለዚህም ቢሮው ተገቢውን ድጋፍ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል ።

በተለይ በድንገተኛ አደጋ ምክንያት የሚጠፋውን የሰው ህይወት ለመታደግ ማዕከሉ የላቀ ሚና እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሙሐመድ ጉዬ ናቸው።

ከመደበኛ የጤና አገልግሎት በሻገር የድንገተኛ አደጋ ተጎጂዎች ፈጣን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መመቻቸቱ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግሯል ።

አስተዳደሩ በተለይ በቂ የህክምና መሳሪያ ፣ አምቡላንሶችና የድንገተኛ ህክምና ባለሙያዎች የማሟላት ስራ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም