የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማሻሻያ ተደረገ

1733

መስከረም 19 ቀን 2015 (ኢዜአ)የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማሻሻያ መደረጉን የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዚሁ መሠረት ከመስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም እኩለ ሌሊት 6:00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ የሚከተለው እንዲሆን ተወስኗል።

1. ቤንዚን በሊትር - 57 ብር ከ05 ሣንቲም

2. ነጭ ናፍጣ በሊትር - 59 ብር ከ90 ሣንቲም

3. ኬሮሲን በሊትር - 59 ብር ከ90 ሣንቲም ሆኗል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሥራ ላይ የነበረው ዋጋቸው ባለበት የሚቀጥል የነዳጅ ውጤቶችንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በዚህም መሠረትየአውሮፕላን ነዳጅ በሊትር - 76 ብር ከ87 ሣንቲም፤ ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር - 43 ብር ከ89 ሣንቲም፤ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር - 43 ብር ከ06 ሣንቲም ሆኖ ይቀጥላል።

ከነደጅ ድጎማ ጋር በተያያዘም አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ በተረዘጋው የታለመ ድጎማ አሠራር ታቅፈው ሕዝቡን እንዲያገለግሉ የተመረጡት የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች በሚጠቀሙት ነዳጅ ላይ በሁለተኛው ምዕራፍ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አልተደገረም።

እነዚህ ተሽከርካሪዎች በሐምሌ ወር በተወሰነላቸው ዋጋ ቤንዚን በብር 41.26 በሊትር እንዲሁም ነጭ ናፍጣን በብር 40.86 በሊትር እየገዙ እንዲቀጥሉ ብቻ ሳይሆን ከእጥፍ በላይ ያደገ ድጎማ ከመንግሥት እንዲያገኙ የተደረገ ስለሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ዋጋ እስኪሻሻል ድረስ በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ምንም ዓይነት ጭማሪ አይደረግም ሲል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም