የሰሜን ወሎ ዞን ህዝብ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የደጀንነት ሚናውን እየተወጣ ነው

266

ወልዲያ፤ መስከረም 18/2015(ኢዜአ)፡- የሰሜን ወሎ ዞን ህዝብ አካባቢውን ከሰርጎ ገቦች ነቅቶ በመጠበቅና በስንቅ ዝግጅት ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የደጀንነት ሚናውን እየተወጣ መሆኑ ተገለጸ።

ከዞኑ  ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ  ህብረተሰብ ተወካዮች በወቅታዊ ጉዳዮች ዛሬ በወልድያ ከተማ ተወያይተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የሰሜን ወሎ ዞን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ሙስጠፋ እንዳሉት፤ ህዝቡ ከአካባቢው የጸጥታ አካላት ጋር  በመተባበር አሸባሪው ህወሃት የሚልካቸውን ሰርጎ ገቦች በመከታተልና በመቆጣጠር  ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ በትኩረት እየሰራ ነው።

በተለይም  በግንባር ለሚፋለመው ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት  ስንቅና ሌሎችንም  ድጋፎችን በማድረግ የደጀንነት ሚናውን እየተወጣ  እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት የከፈተው ጦርነት የመመከቱ ስራ በግንባር ብቻ ሳይሆን በውስጥ ሰርገው ከሚገቡ ተላላኪዎች ጭምር በመሆኑ መላው ህዝብ ከተማውንና አካባቢውን ነቅቶ መጠበቁን አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዞኑ ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ድጋፍም እንዲሁ።

የወልድያ  ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ዳዊት መለሰ በበኩላቸው፤  ህይወቱን ሳይሰስት እየሰጠ የሀገሩን ሉአላዊነትና የህዝብ ደህንነት ለሚያስጠብቀው ሠራዊታችን ታላቅ ክብር አለን ብለዋል።

መላ የከተማውና የአካባቢው ህዝብም ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት  ግንባር ድረስ በመዝመት ስንቅ  በማቅረብ እያደረገ ያለው እገዛ የሚበረታታ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዚህ በተቃራኒው አብረው እየኖሩ ለአሸባሪው ህወሃት መረጃ በመስጠትና ሌሎች ትብብሮችን የሚያደርጉ ግለሰቦችን ህብረተሰቡ በመከታተል በአካባቢው ለሚገኝ የጸጥታ ሃይል መጠቆም አለበት ብለዋል።

የአማራ ክልል በይነ መንግስታት ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ደስታ ተስፋው፤  የጠላት ዋና ዓላማው በህዝባዊ ማዕበል መንግስትና ህዝብን በማስጨነቅ ሀገር ማፍረስ መሆኑን ሁሉም መገንዘብ እንዳለበት ተናግረዋል።

ሴራው የኢትዮጵያን አንድነት፣ እድገትና ብልጽግና መቼም በማይመኙ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ተቀነባብሮ በሽብር ቡድኑና ተላላኪዎቹ የሚፈጸም ነው ብለዋል።

ሰርጎ በሚያስገባቸውና በውስጥ ካሉ ቅጥረኞች በሚነዙት የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ታግዞ አሸባሪው የከፈተው ሶስተኛው  ዙር ጦርነት  አሁን ላይ በህዝብ የደጀንነት ድጋፍና በጅግናው መከላከያ ሰራዊት እየከሸፈ መምጣቱን ገልጸዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ወጣቶችም በደጀንነት የሚያከናውኑት ስራ   አኩሪ መሆኑን አስታውቀዋል።