የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አመራርና ሠራተኞች “ደማችንን ለመከላከያ ሠራዊታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ደም ለገሱ

224

መስከረም 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አመራርና ሠራተኞች “ደማችንን ለመከላከያ ሠራዊታችን” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ የደም ልገሳ መርሃ-ግብር አካሂደዋል።

የኢዜአ ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሮች ከዚህ ቀደም ከአሥር ጊዜ ላላነሰ ደም ለግሰዋል።

የዛሬው ደም ልገሳ መርሃ-ግብር ለሠራዊታችን ሕዝባዊ ደጀንነታችንን ያረጋገጥንበትና አብሮነታችንን ለማሳየት የተከናወነ ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ የአገር ሉዓላዊነትን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እያበረከተ መሆኑን አንስተው፤ ከዚህ  አኳያ ኀብረተሰቡ ሠራዊቱን ሊደግፍና ሊያጠናክር ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዚህ ረገድ ትናንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅን ጨምሮ አርቲስቶችና በተለያዩ የስራ መስኮች የተሰማሩ ሙያተኞች ሰራዊቱን በመደገፍ ረገድ ያከናወኑትን ተግባር አድንቀዋል፡፡

ለመከላከያ ሠራዊት የሚደረግ ድጋፍ ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅ የሚፈጸም አኩሪ ተግባር መሆኑንም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚው የገለጹት፡፡

በኢዜአ የሕዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክተር ዮሐንስ ወንድይራድ በበኩላቸው ተቋሙ በተለያዩ ጊዜያት ባካሄደው የደም ልገሳ መርሃ-ግብር መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ዛሬም መከላከያ ሠራዊት ጎን መሆናቸውን ለማሳየት ደማቸውን መለገሳቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ለሠራዊቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የሚዲያ ባለሙያዎች ደም ከመለገስ ባሻገር ሕብረተሰቡ ደም ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች እንዲለግስ የመቀስቀስና የማስገንዘብ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም ነው የገለጹት።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሴቶችና ባለብዙ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ታደለች ቦጋለ በበኩላቸው፤ ተቋሙ በየሦስት ወሩ በቋሚነት የደም ልግሳ መርሃ-ግብር እንደሚያካሂድ ገልጸዋል።

በዚህም የአገልግሎቱ አመራርና ሠራተኞች ደም ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የአቅማቸውን እያበረከቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሠራዊቱ የሚደረገው የደም ልገሳም እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

የኢዜአ የአረብኛ ክፍል ከፍተኛ ሪፖርተር አህላም መሀመድ አህመድ የማይተካ ህይወቱን ከፍሎ አገርና ሕዝብ ለማዳን ለሚፋለመው የመከላከያ ሠራዊት ደም በመለገሷ ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።

ኢትዮጵያ የተከፈተባትን ባለብዙ ፈርጅ ጦርነት እንድታሸንፍ ሁሉም በየዘርፉ ሚናውን መወጣት እንዳለበትም ጥሪ አቅርባለች፡፡

በተመሳሳይ የተቋሙ ከፍተኛ የግዢ ባለሙያ የሆኑት አቶ ካሳሁን አሊ ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ደም መለገሳቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

ደም መለገስን ባህል በማድረግ ወገናዊ አለኝታነትን በተግባር መወጣት እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም