ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ነው

352

መስከረም 18/2015 /ኢዜአ/የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ህልፍተ ህይወትን ተከትሎ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የተሰማቸውን ሀዘን እየገለጹ ይገኛሉ።

ሀዘናቸውን ከገለጹ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች መካከል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አንዱ ናቸው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሀዘን መግለጫቸው አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ለሀገሩና ለትውልድ ጥበብንና ባህልን አውርሶ ያለፈ እውቅ ከያኒ መሆኑን ገልጸው የሚችለውን ሁሉ ለሚወዳት ሀገሩ ተቀኝቷል ብለዋል፡፡

በችግር ውስጥ ሆኖም ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር ሲል ከጠላት ጋር የሚዋደቀውን ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንን እና የጸጥታ ኃይላችንን ግንባር ድረስ ዘልቆ አበረታትቷል ሲሉም ገልጸዋል።

ስለኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔና ታሪክ፣ሰላምና አንድነት፣ነጻነትና ክብር በርካታ የጥበብ ሥራዎችን መሥራቱን ጠቁመው ለቤተሰቦቹ ለአድናቂዎቹ እና ለሙያ አጋሮቹ መጽናናትን ተመኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው በአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ህልፈተ ህይወት 'ከልብ አዝኛለሁ' ብለዋል።

''ለቤተሰቦቹ ፣ለወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ መጽናናትን እመኛለሁ።ፈጣሪ ነብሱን በአጸደ ገነት ያኑር'' ሲሉም ሀዘናቸውን ገልጸዋል።ማዲንጎ የተዋጣለት ከያኒ ብቻ ሳይሆን ልበቀናና ሀገር ወዳድ ነበር ያሉት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ናቸው፡፡

አምባሳደሩ የአርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ ሕልፈተ ሕይወት እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነው ካሉ በኋላ ማዲንጎ እንደሰው ሰከን ያለ ሰብዕና የተላበሰ ሰው እንደነበር ገልጸው ሕልፈተ ሕይወቱ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ነው በማለት ሀዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ድንገተኛ ህልፈት መስማት በእጅጉ ያስደነግጣል ያሉት ደግሞ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ናቸው።

አምባሳደር ስለሺ አክለውም ማዲንጎ በሙያው ለአገሩ ሰፊ አበርክቶ ያለው፣ሁሌም ለአገሩ ጥሪ ቀድሞ የሚደርስ ትሁትና የተዋጣለት ባለሙያ ነበር ብለዋል።

ለቤተሰቦቹ እና ለወዳጆቹ መጽናናትን እመኛለሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።በካናዳ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው በወጣቱ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ድንገተኛ ህልፈት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶኛል።

ታላቅ ሀገር ወዳድ አርቲስት አጥተናል በማለት ለቤተሰቦቹ፣ለወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናት እንዲሆን ጸሎቴ ነው ብለዋል።

በድምጻዊው ህልፈተ ህይወት ምክንያት የሀዘን መልዕክት ካስተላለፉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች መካከል የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፣ የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ ይገኙበታል።

የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ የአፋርን ባህል፣ውበት እና የተፈጥሮ ሀብት ያስተዋወቀ፤ ለአፋር ህዝብ የለውን ፍቅር በሙዚቃው ያቀነቀነ ድንቅ አርትስት ነው በማለት በአርቲስቱ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማንን ሀዘን ለመግለጽ እንወደዋለን ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አርቲስት ማዲንጎ አፈወርቅ በማረፉ የተሰማኝ ኀዘን ከባድ ነው።

ለሀገሩ በአጭር እድሜው ብዙ የሠራ ከያኒ ነው፤ ሀገር በተደፈረች ጊዜ ሕመሙን እየቻለ ግንባር ተገኝቶ ሠራዊቱን ማጀገኑን እንዲሁም ሠልጣኞችን ማበረታታቱን በመግለጽ ነፍሱ በሰላም ትረፍ በማለት ሀዘናቸውን ትላንት መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም