ሪፖርቱ የህወሓትን ጥቅም ለማሰጠበቅና ምዕራባዊያን በአፍሪካ ቀንድ ያላቸውን ጣልቃ ገብነት ለማስቀጠል ያለመ ነው- ምሁራን

90

ዲላ መስከረም 18/2015 (ኢዜአ) የኮሚሽኑ ሪፖርት በሰብዓዊነት ሰም የአሸባሪውን ህወሓት ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅና ምእራባዊያን በምስራቅ አፍሪካ ያላቸውን ጣልቃ ገብነት ለማስቀጠል ያላቸውን ዓላማ ያረጋገጠ መሆኑን የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የባለሙያዎች ቡድን ከሰሞኑ ያወጣው ሪፖርት በሰብአዊነት ሰም የአሸባሪውን ህወሓትን ጥቅም ለማስጠበቅና ምእራባዊያን በምስራቅ አፍሪካ ያላቸውን ጣልቃ ገብነት ለማስቀጠል ያለመ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስከበርና መሰል የውጭ ተጽዕኖን ለመቋቋም ደግሞ ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ በመስራት አገሩን በኢኮኖሚ ማሳደግ እንደሚገባም አመላክተዋል ምሁራኑ።

ከሰሙኑ አድሏዊ ሪፖርት ተከትሎ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን መካከል በዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍ ህግ መምህር አማኑኤል ታደሰ ሪፖርቱ "የኢትዮጵያን የሰላም ጥረት ከግምት ያላስገባ ነው" ብለዋል።

ሪፖርቱ ለአሸባሪው ቡድን ከማድላቱ ባለፈ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከ1 ዓመት በፊት ከኢትዮጰያ ሰብዓዊ መብት ጋር በመተባበር ያወጣውን ሪፖርት ጭምር ያጥላላ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ህብረቱም ሆነ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ የአባል ሀገራትን መብት በአንድ ዓይን የማየት ግዴታ ቢኖርባቸውም ከፍተኛውን ቀለብ የሚሰፍሩለት ሀገራት ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀ መሆኑን የሚያሳዩ ድርጊቶችን በተደጋጋሚ እየፈጸመ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በዚህም ሪፖርቱ በሰብዓዊነት ሽፋን የህወሓትን ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅና ምእራባዊያን በተለይ አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት በምስራቅ አፍሪካ ያላቸውን ጣልቃ ገብነት ለማስቀጠል ያለመ ነው ብለዋል።

የውጭ ሃይላት የሚፈጥሩትን ጫና በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችል የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ደግሞ ከመሰል ጫናዎች አገሪቷን እንደሚታደግም አመላክተዋል መምህር አማኑኤል።

በተለይ በምግብ ሰብል እራሳችንን መቻል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግስት በግብርና ልማት የጀመረው ጥረት ከዳር እንዲደርስ የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሪፖርቱ አንዳንድ የምዕራብ ሃገራት ኢትዮጵያን በሃይል ለመጠምዘዝ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ በገሃድ ያሳየ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጭ በዩኒቨርሲቲው የብዝሃ ባህልና አስተዳደር ጥናት መምህር ሄኖክ ንጉሴ ናቸው።

በእርግጥ ኮሚሽኑ ገለልተኝነትን ለማስፈን በሚል ኤክስፐርቶች ከተለያዩ አገራት ቢሰይምም ይዘውት የመጡት ሪፖርት የይዘት ችግርና ያለውና ለአንድ ወገን ያደላ የፖለቲካ ፍላጎት ያመዘነበት መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም የህወሓት ዕድሜን ለማስረዝም የሚደረግ የጥረት አካል ከመሆኑ ባለፈ የምእራባዊያን ሀገራት በአፍሪካ ቀንድ ያለቸውን የተለመደ ጣልቃ ገብነት ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያዊያን ዕድገትና ልማት የሚያስደነግጣቸው ምዕራባዊያንና ታሪካዊ ጠላቶቻችን በማበር በአሸባሪነት ለተፈረጀው ቡድን ያላቸውን ውግንና ማሳየታቸው የታሪክ ተጠያቂነት ከማስከተሉ በላይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንድታዘበው ያደረገ ነው ብለዋል።

በጦርነት ውስጥ መቆየት ለሀገር ኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት አዋጭ አይደለም ያሉት ምሁሩ የህወሓት ጥቃት ከመከላከል ጎን ለጎን በመንግስት በኩል የሰላም አማራጮች ዛሬም ክፍት መሆኑን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ደጋግሞ ማሳወቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ ምሁራን በሀገራችን ላይ የተከፈተውን የዲፕሎማሲ ጫናዎችን በዘላቂነት ለመመከት ባገኘነው አጋጣሚ የሀገራችንን እውነታ ማሳወቅ አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም